በአለም አቀፍ ደረጃ ገዳይ በሽታዎችን ለመከላከል 11 ቢሊየን ዩሮ ያስፈልጋል ተባለ

93

ጥር 5/2011 በአለም አቀፍ ደረጃ ገዳይ በሽታ የሆኑትን ኤች አይቪ ኤድስ ፣የሳምባ ነቀርሳና የወባ በሽታን ለመከላከል 11 ቢሊየን ዩሮ አዲስ በጀት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ ፡፡

ቢቢሲ ይዞት በወጣው ዘገባ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሶስቱን በሽታዎች ለመከላከል የሚሰራው ግሎባል ፈንድ ጉባኤን በፓሪስ ከፍተዋል፤ጉባኤውም“ወሳኝ ምእራፍ”ተሰኝቷል፡፡

ግሎባል ፈንድ እንዳለው የፖለቲካ ቁርጠኝነት መቀዛቀዝ፣ የፀረ ነብሳትና መድሃኒት የሚቋቋሙ ተሃዋስያን መጨመር በሽታዎቹን የመከላከሉን ሂደት አዝጋሚ አድርጎታል፡፡       

የሚፈልገው ያህል ብር ከተገኘ የ16 ሚሊየን ሰዎችን ህይወት መታደግ ይቻላል በነዚህ ሶስት ገዳይ በሽታዎች የሚሞተውን ሰው ቁጥርም በግማሽ መቀነስ ይቻላል ብሏል ዘገባው፡፡  

11 ቢሊየን ዩሮ (14 ቢሊየን ዶላር) ኤች አይቪን ለመከላከልና ለማከም፣ለሳምባ ነቀርሳ መድሃኒቶችና ወባን ለመከላከል ለአጎበር የሚውል ይሆናል፡፡

የግሎባል ፈንድ ስራ አስፈፃሚ ፒተር ሳንድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “በበሽታዎቹ የሚደርሰውን ሞት በአስደናቂ ሁኔታ  መቀነስ ቢቻልም ሂደቱን ግን ማስቀጠል አልተቻለም “ብለዋል፡፡

ግሎባል ፈንድ ከተለያዩ የካፒታል ምንጮች ገንዘብ እያሰባሰበ መሆኑን ገልፀው የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ላይ ለመድረስ የአለም የፓለቲካ ሁኔታ ውስብስብነት አዳጋች እያደረገው ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን ግሎባል ፈንድ ከመንግስታትና ከለጋሽ ድርጅቶች የሚያገኘውን አለም አቀፍ የጤና ፈንድ ተፅእኖ በሚፈጥር መልኩ  እየተጠቀመበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የሚያጋጥሙ የገንዘብ እጥረቶች በአለም አቀፍ ደረጃ  በሽታዎቹ በወረርሽኝ ደረጃ እንዳይከሰቱ  የተደረሰውን  ሶስተኛ  ዘላቂ የልማት ግብ ስምምነት ስጋት ላይ የሚጥል እንደሆነውም ሳይጠቅሱ አላለፉም ፡፡

የወባ ታማሚዎች ቁጥር ቀንሶ ከነበረበት ሁኔታ እየጨመረ እንደሆነ የገለፀው ዘገባው በወባ ከሚሞቱ ሁለት ሶስተኛው እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑት ህፃናት ናቸው፡፡

የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒቶች ሚሊየኖችን ከሞት የታደጉ ቢሆንም  በአፍሪካ አዳዲስ ለኤች አይቪ የሚጋለጡ ወጣቶች ቁጥር መጨመርም አሳሳቢ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የሳምባ ነቀርሳም ከሌሎች ኢንፌክሽኖች በላቀ ሰዎችን እየገደለ ሲሆን መድሃኒቱን በተላመደ ህዋስ ሳቢያም በአለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ታማሚዎች  አንድ ሶስተኛው ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡

የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም  ግሎባል ፈንድ ባለፉት 17 አመታት በጤናው ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም