''ወጣቱ ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ስልጣኔዋ ለመመለስ ለሰላም ዘብ መቆም አለበት''-ፕሮፌሰር ፍቅሬ

53

ደብረማርቆስ ጥር 5/2011 ወጣቱ ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ስልጣኔዋ ለመመለስ ታሪኩን አውቆ ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ገለጹ፡፡

"የአስተሳሰብ አብሮነት መልካም ነገርን ለማየት" በሚል መሪ ቃል የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ከታዋቂው ደራሲና ገጣሚ ጋር ተወያይተዋል።

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ወጣቱ የአገሩን የቀደመ ታሪክ ማወቅና ለአብሮነትና አንድነት የሚጠቅሙ እሴቶችን እንዲያጠናክር አስገንዝበዋል፡፡

የተጀመረው አራዊ የለውጥ ጉዞ ውጤታማ የሚሆነው ወጣቱ በሰከነ መንገድ የአገሩን ሰላም ሲጠብቅና ሲያከብር ነው ብለዋል፡፡

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች የግለሰቦች የጥቅም ግጭት እንጂ ፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች መገለጫዎች አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የተረጋጋ ሰላም እንዲኖርና የኢትዮጵያውያን አንድነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲጸና ወጣቶች በአስተውሎ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም ፕሮፌሰር ፍቅሬ አሳስበዋል።

ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተማሪ ይርጋለም ኃይሌ ከምሁሩ በቂ የታሪክ ትምህርት አግኝቻለሁ ይላል። በአስተሳሰብም ሆነ በትምህርት የበሰሉ ምሁራን መድረኮችን በመጠቀም ወጣቱን ማስተማራቸው አለመግባባቶችን እንደሚፈታ ተናግሯል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህር አወቀ ዓሊ በውይይቱ ያገኙት ግንዛቤ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ያላቸውን ማህበራዊ ትስስር እንደሚያጠናክርላቸው አመልክተዋል።

የዩኒቨርስቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ገነት ደጉ በበኩላቸው የኢትዮጵውያን መገለጫ ባልሆኑት በዘር፣ በሃይማኖትና በጎጥ መከፋፈልን በመተው ለሰላም  ዘብ እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

አንድነትን በማጠናከር በጋራ ለመስራት የኢትዮጵያን የቀደመ ታሪክ ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እንደአገር የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የተረጋጋ ሰላምና አንድነት ለመፍጠር መትጋት አለባቸው ብለዋል።

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም