በእግር የመጓዝ ባህል ጤንነትን ለመጠበቅ ያግዛል

65

አዲስ አበባ ጥር 5/2011 መንገዶችን ከተሽከርካሪ ነጻ በማድረግ የተጀመረው ስፖርታዊ መርሃ ግብር በህብረተሰቡ ዘንድ በእግር የመጓዝ ባህልን በማዳበር የዜጎችን ጤንነት ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ተገለፀ።

በአዲስ አበባና በተመረጡ የክልል ከተሞች ከተሸከርካሪ ፍሰት የፀዱ የመንገዶች ቀን ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ነው።

ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ላይ መንገዶቹ ከተሽከርካሪ ነጻ ሆነው ነዋሪዎች የእግር ጉዞና የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማከናወናቸው ይታወሳል። 

መርሃ ግብሩ በየወሩ አንድ ቀን በቋሚነት ይከናወናል ተብሏል።

በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተሽከርካሪ እንቅስቃሴ በፀዱ መንገዶች ላይ በተከናወነው የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የእግር ጉዞ መርሃ ግብር ላይ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው በሰጡት አስተያየት የዚህ ዓይነቱ መርሃ ግብር ዜጎች የእግር ጉዞን ባህላቸው አንዲያደርጉ፤ በዚህም በአሁኑ ወቅት እየተስፋፉ የመጡትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ያግዛል ሲሉ ገልፀዋል። 

አቶ ቢተው ደመላሽ እና  ወይዘሮ ቁምነገር ጌታቸው እንደሚሉት በከተማው የህብረተሰቡ በእግር የመጓዝ ባህል ዘቅተኛ ከመሆኑም በላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን የሚያስችል የተመቸ ቦታ የለም፤ መርሃ ግብሩ ይህንን ሁኔታ ለማሻሻል ያግዛል።

"መንገዶች በትራፊክ በተጨናነቁባት አዲስ አበባ ነዋሪዎች የ1ብር ከ50 ሳንቲም መንገድ እንኳን በእግሩ ለመሄድ አይፈልግም ፣ አሁን ግን በዚህ መልኩ መንገድ ዝግ ተደርጎ እንቅቃሴዎች መጀመራቸው ሰዎች በእግር የመሄድ ባህልን ያዳብራሉ" ሲሉ ወይዘሮ ቁምነገር ተናግረዋል።

ወይዘሮ መሃቡባ ሰማን በበኩላቸው፣ በከተማዋ ይህ አይነቱ ከትራፊክ ነጻ የሆነ መንገድ በየወሩ መፈጠሩ መልካም ቢሆንም በየ15 ቀኑ ቢደረግ የተሻለ ውጤታማ ይሆናል ሲሉ ነው የገለፁት።

የልደታ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማው ማሙያ ጤንነቱን በራሱ መጠበቅ የሚችል ዜጋን ለማፍራት ታስቦ የተጀመረው መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ግንዛቤ ለማስፋት እንደሚያስችል ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ባለፈው ወር በከተማ ደረጃ የተጀመረው ከትራፊክ ፍሰት ነጻ የሆነ መንገድ ዛሬ በአራት ክፍለ ከተሞች ተከናውኗል።

በልደታ ክፍለ ከተማ ከብሄራዊ ቲአትር እስከ ልደታ ቤተክርስያን ያለው ጎዳና ዛሬ ለሙሉ ቀን ከተሽከርካሪ ነፃ የተደረገ ሲሆን በርካቶች የተሳተፉበት የእግር ጉዞና የአካል ብቃት እንቅስቃሴም ተከናውኗል።

መንገዶቹም ቀኑን ሙሉ ከተሽከርካሪ ነጻ መደረጋቸው መንገዶቹን የሚጠቀመው ነዋሪ በእግሩ እንዲጓዝ እድል ፈጥሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና አጋላጭ መንስኤዎቻቸውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ህብረተሰቡ የመመርመር ልምዱን ሊዲያዳብር እንደሚገባም ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ በየአመቱ ከሚሞተው ሰው 52 በመቶው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

መርሃ ግብሩ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በዛሬው እለት በባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ መቀሌ፣ ጅጅጋ እና ድሬዳዋን ይከናወናል ተብሏል።

መርሃ ግብሩ በወር አንድ ቀን ወሩ በገባ የመጨረሻውን እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተመረጡ መንገዶችን ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ በማድረግ የሚካነወን ይሆናል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም