በደቡብ ወሎ ዞን ከ91 ሺ በላይ ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ ነው

165

ደሴ ጥር 5/2011 በደቡብ ወሎ ዞን በተያዘው የበጋ ወቅት 91 ሺህ 230 ሄክታር መሬት በመስኖ እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬ የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ ሰይድ አህመድ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በእቅድ ከተያዘውም እስካሁን 37 ሺህ ሄክታር መሬት በባህላዊና ዘመናዊ መንገድ ለምቷል።

ቀሪውን መሬት ለማልማትም የመኸር ሰብልን የመሰብሰብና የእርሻ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመስኖ ልማቱ ከ302 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ለልማቱ ከ25 ሺህ ኩንታል በላይ ማደበሪያና 124 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሰራ ይገኛል።

አርሶ አደሩ ባመረተው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን ከተለያዩ ዩኒቨረሲቲዎች፣ ሆቴሎችና ባለሀብቶች ጋር የተፈጠረውን የገበያ ትስስር ለማጠናከርም እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በለጋ አምቦ ወረዳ የ020 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ስዩም አዘነ  በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ወንዝ በመጥለፍ ገብስ፣  አብሽና ስንዴ ለማምረት የእርሻና የዘር ስራ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ ግብዓቶችን ተጠቅመው በሁለት ዙር ከ30 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የባለሙያን ምክረ ሃሳብ ተግባራዊ በማድረግ ዘመናዊ የውሃ አጠቃቀም ዘዴን እንደሚከተሉ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ባካሄዱት የመስኖ ልማት እንቅስቃሴ ከሰብል ምርት ሽያጭ 30 ሺህ ብር ገቢ እንዳገኙም አስታውቀዋል።

በከላላ ወረዳ የ032 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሃመድ አሊ በበኩላቸው በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ አብሺ፣ ጎመንና ጓያ ለማምረት ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ከ20 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ያቀዱ ሲሆን እስካሁን ሩብ የሚሆነውን ማሳ ማልማታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ አጠቃላይ በመስኖ ከሚለማዉ መሬት ውስጥ 14 ሺህ ሄክታር የሚጠጋው በኩታ ገጠም የሚለማ ሲሆን ከ11 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም