በሐዋሳ የድንገተኛ አደጋዎችና የቀዶ ጥገና ስፔሻላይዝድ ህክምና ማዕከል ተመረቀ

78

ሐዋሳ ጥር 5/2011በሐዋሳ ከተማ የድንገተኛ አደጋዎችና የቀዶ ጥገና ስፔሻላይዝድ ህክምና ማዕከል ትናንት ተመረቀ።

ማዕከሉ ባለ 11 ወለል ህንጻ የህክምና አገልግሎት ለሚሰጥበት ሆስፒታል የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የክልሉ መንግሥት የኅብረተሰቡን የጤና ፍላጎት ለማሟላት ለባለሀብቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የግል ባለሀብቶች መከላከልን መሠረት ባደረገው የጤና ፖሊሲ በጤናው ዘርፍ ለተገኙ ውጤቶች ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

ባለሀብቶቹ በዘርፉ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለኢንቨስትመንት የሚሆን መሬት እንደሚሰጣቸውም አመልክተዋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት 4ሺህ 670 የጤና ተቋማትን መገንባታቸውንና ለነዚህም በሰው ኃይልና በቁሳቁስ በማሟላት በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ዕድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ በበኩላቸው ማዕከሉ በድንገተኛ አደጋዎች የሚከሰተውን ሞትና የአካል ጉዳት ለመቀነስ  እንደሚያስችል ገልጸው ፣ በመስኩ ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላት  ማዕከሉ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

የያኔት የድንገተኛ አደጋዎችና የቀዶ ጥገና ስፔሻላይዝድ ህክምና ማዕከል ባለቤት ዶክተር ግርማ አቢ እንዳሉት ማዕከሉ በኢትዮጵያ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሶስተኛ ደረጃ በገዳይነቱ የሚታወቀውን የመኪና አደጋንና ሌሎች አደጋዎችን እንደሚያክም አስታውቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ማዕከሉ ባለ 11 ወለል ህንጻ የህክምና አገልግሎቶችን በአንድ ላይ ለሚሰጥበት ሆስፒታል የመሠረት ድንጋይ በርዕሰ መስተዳድሩ ተቀምጧል።

የሆስፒታሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ 700 ለሚሆኑ ዜጎች ሥራ እንደሚፈጥርና ሀዋሳን የህክምና ቱሪዝም ማዕከል እንደሚያደርጋት ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የድንገተኛ አደጋዎች ህክምና የሚሰጥ የጤና ተቋም በአዲስ አበባ የተቋቋመው አቤት ሆስፒታል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም