የአፋር ክልል ምክር ቤት የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር ከአጎራባች ክልል ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

1345

ሰመራ ጥር 4/2011 የአፋር ክልል ምክር ቤት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከአጎራባች ክልል ምክር ቤቶችጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡

የአፋርና ትግራይ ክልል አጎራባች ወረዳ ምክር ቤቶች የጋራ ፎረም ዛሬ በሰመራ ከተማ ተካሄዷል፡፡

በዚህ ወቅት የአፋር ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወይዘሮ አሚና ሴኮ እንደተናገሩት የአፋር አርብቶ አደር ህብረተሰብ ከአጎራባች ክልል ህዝቦች ጋር አብሮ በሰላም የመኖር ባህላዊ እሴቶች አሉት፡፡

ይህንን በመጠበቅ በጋራ ለመልማት  በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በትኩረት ሊሰራ ይገባል፡፡

ከዚህ አንጻር የአፋር ክልል ምክር ቤት ከአጎራባቾቹ ትግራይ፤ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ምክር ቤቶች ጋር ባለፉት ዓመታት የህዝብ ውክልናውን በአግባቡ ለመወጣት እንዲረዳው የጋ ራ ፎረም ማዘጋጀቱን አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ተሞክሮ በመለዋወጥና በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች በመከላከልና በመቆጣጣር አበረታች ሰራዎችን መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

አለአስፈላጊ ግጭቶችና ሌሎች ህገወጥ ተግባራት ተወግደው የህዝቦች አብሮነት እንዲጎለብትና  በልማት እንዲተሳሰሩ መልካም አጋጣሚዎች መፈጠሩን አመልክተዋል፡፡

በቀጣም በሀገሪቱ የተጀመሩ የለውጥ ጉዞ የህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ እንዲረጋገጥ ፣ ለዘመናት የገነቧቸው አብሮነት እንዲጠናከር  ከአጎራባች ክልል ምክር ቤቶች ጋር ተቀራርበው እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ሩፋኤል ሽፈራዉ በበኩላቸው ባለፉት ስምንት ዓመታት በሁለቱ ክልል ምክር ቤቶች መካከል ተሞክሮዎቻቸው በመለዋዋጥ ሲደጋገፉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

አልፎ አልፎ በአዋሳኝ አካበቢዎች በግጦሽ ሳርና ተያያዥ ጉዳዮች ይፈጠሩ የነበሩ ግጭቶችን  ለማስቀረት ምክር ቤቶቹ  አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡  

አቶ ሩፋኤል እንዳመለከቱት ለዘመናት የገነቡት አብሮነትና የመረዳዳት ባህሎች ጎልበተው  ሰላምን ከማረጋገጥ አልፈው በልማት እየተሳሰሩ ድህነትን ለማሸነፍ  እየተጉ ነው፡፡

በክልልና ወረዳ ምክር ቤት ደረጃ የተጀመሩ የጋራ ፎረሞች እስከቀበሌ መዋቅሩ ድረስ አጠናክሮ በመዘረጋት ህብረተሰቡ የበለጠ የልማቱ  ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመሩትን ስራ እንደሚያናክሩም አረጋግጠዋል፡፡

በአፋር ክልል የያሎ ወረዳ ዋና አፈጉባኤ አቶ ሞሚን ሁሴን ከአጎራባች ራያ አዘቦና ራያ አላማጣ ጋር ባለው የጋራ ትብብር ፎረም  የሚያጋጥሙ ጥቃቅን ችግሮችን በቀላሉ በፍጥነት በመፍታት ህብረተሰቡ ሰላሙ ዋስትና እንዲኖረው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች  የተሳሰሩ ወንድማማች ህዝቦች በክፉም ሆነ በደጉ እየተደጋገፉ አብረው እየኖሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በትግራይ ክልል የራያ-አላማጣ ወረዳ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አበባ ሲሳይ ናቸው፡፡

በተለይም በደርቅ ወቅት የአፋር ወንድሞቻቸው  የቤት እንስሳቶቻቸውን በራያ አላማጣ የተለያዩ አካበቢዎች እየመጡ አብረው በፍቅርና በሰላም ሳርና ውሃ በጋራ እንደሚጠቀሙ አውስተዋል፡፡

የራያ- አላማጣም ወንድሞቻቸው በተመሳሰሳይ   ችግር ሲጋጥማቸው ወደ አፋር አጎራባት ያሎና ሌሎች ወረዳዎች ድረስ ከብቶቻቸውን  እየወሰዱ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል፡፡

የጋራ ፎረሙ  ያለፉት ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸምን  በመገምገም የቀጣይ እቅድና የትኩረት አቅጣጫ ላይ ተወያይቷል፡፡