ክልሎች ብሔራዊ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የሚያደርግላቸው ድጋፍና ክትትል አነስተኛ እንደሆነ ገለጹ

87

አዲስ አበባ ጥር 4/2011 የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ለክልሎች የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል አነስተኛ እንደሆነ የክልል የወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የስራ ሃላፊዎች ገለጹ።

20ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ በአዲስ አበባ ያካሄደው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ክልሎችን በበቂ መጠን እየደገፈ እንዳልሆነ አምኗል።

የኦሮሚያ ክልል ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታምራት ፈይሳ እንደገለጹት፤ ፌዴሬሽኑ በቁሳቁስ፣ በቴክኒክና በስልጠናዎች ለክልሉ ድጋፍ እያደረገ አይደለም።

አሰልጣኞችና ዳኞች እንዲጎለብት የሚያስችሉ ስልጠናዎችም በበቂ ሁኔታ ለመስጠት የሚያስችላቸውን የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ከሟሟላት አንጻርም ሰፊ ክፍተት እንዳለ ጠቅሰዋል።

ፌዴሬሽኑ ክልሎችን በመገምገም የሚጎድላቸውን ነገር ለሟሟላት በበቂ መጠን እየሰራ አለመሆኑን ገልጸዋል። የሚያደርገው ክትትል ዝቅተኛ በመሆኑ ስፖርቱን ከማስፋፋት አንጻር ችግር እየፈጠረ እንደሆነ ተናግረዋል።

''ፌዴሬሽኑ በየክልሉ ያሉ ፕሮጀክቶች እንዲያድጉ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል'' ብለዋል።

የአማራ ክልል ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አማን ሞላ በበኩላቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለክልሉ የሚያደርገው ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን አንስተዋል።

በአጠቃላይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከክልሎች ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር የሚያስችለውን አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ተወዳዳሪዎች በቁሳቁስ ባለመደገፋቸው ልምምድ ሰርተው ውድድር ላይ ሲመጡ እየተቸገሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የጋምቤላ ክልል ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አቡላ አጄየር እንዳሉት፤ በክልላቸው ውድድር ሲካሄድ ብቁ የሆነ ዳኛ ባለመኖሩ የዳኝነት የውሳኔ ችግሮች እያታዩ ነው።

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ወደ ክልሉ መጥቶ የዳኝነት ስልጠና በመስጠት ብቁ ዳኞች እንዲፈሩ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

ህገወጥ የአሰልጣኝነት የ'ዳን' ፈተና አሰጣጥ ያለው ጉዳይ መፍትሄ ማግኘት አለበት፣ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት፣ የውድድሮች ቁጥር ማደግ አለበትና ስፖርቱ እንዲስፋፋ የንቅናቄ ስራዎች መሰራት አለባቸው የሚሉ ሃሳቦች በጉባኤው ተነስተው ፌዴሬሽኑ ክልሎችን እንዲደግፍ ተጠይቋል።

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አትናቲዎስ መልዐከሰላም ለክልሎች የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል አነስተኛ መሆን ድክመቱ እንደሆነ አምነው ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፉ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የሚመጣለትን ቁሳቁስ ለክልሎች እያሰራጨ እንደሆነ ገልጸው ድጋፉ በቂ ባለመሆኑ በክልሎች ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

አማራጭ የሀብት አሰባሰብ መንገዶችን በመከተልና ከስፖርት ኮሚሽኑና ከዓለም አቀፉ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለማበጀት እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።

ህገወጥ የዳን ፈተናን ችግሩን መፍታት የሚያስችል ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑንና በ15 ቀን ውስጥ ድንቡ ተጠናቆ ለክልሎቹ እንደሚላክ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት አስፋው ፌዴሬሽኑ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ጠቅላላ ጉባኤ አለማካሄዱ ለክትትሉና ድጋፉ ማነስ መንስዔ መሆኑን ገልጸው ከዚህ በኋላ ፌዴሬሽኑ ወቅቱን ጠብቆ ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያካሂድ ጠቅሰዋል።

ክልሎችም ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጋር ተቀራርቦ ከመስራት አንጻር ክፍተት እንዳለና ከክልሎችም በጋራ አንድ ላይ ከስፖርት ፌዴሬሽኑ ጋር መስራት አለባቸው ብለዋል።

''ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቱን የማጠናከር ስራ፣ ውድድሮችን ማብዛት፣ ስልጠናና የቁሳቁስ ድጋፍ ጉዳይ፣ ስፖርቱን ማስፋፋት የሚያስችል ውይይቶችና ስራዎችን ማከናወን ፌዴሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ዋንኛ ትኩረት የሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው'' ብለዋል።

በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ብቁ ስፖርተኛ ለማፍራት ክልሎች የሚጠበቅባቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸውና በአጠቃላይ ለስፖርቱ እድገት ከመለያያት ይልቅ አንድ ሆኖ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በጉባኤው ማብቂያ የሁለት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የማሟያ ምርጫ ሊካሄድ የነበረ ቢሆንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብቻ እጩ በማቅረቡ ጠቅላላ ጉባኤው ከዚህ በፊት በ2008 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ሲካሄድ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ተጠባባቂ የነበሩ ሁለት ሰዎች ይመረጡ ብሏል።

በዚሁ መሰረት በ2008 ዓ.ም ተጠባባቂ የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እጩ አቶ አለማየሁ ጌታቸው የስራ አስፈጸሚ ኮሚቴ አባል ሆነው የተመረጡ ሲሆን ሌላኛው ተጠባባቂ ፈቃደኛ መሆናቸው ተጠይቆ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አባል እንዲሆኑ ተወስኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም