የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ሃገርን ከመገንባት አኳያ ክፍተት ያለበት ነው...የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

178

አክሱም ጥር 4/2011 በሀገሪቱ ያለው የመገናኛ ብዙሀን አጠቃቀም ሀገርን ከመገንባትና የማህበረሰቡን የጋራ አስተሳሰብ ከመቅረጽ አኳያ ክፍተት ያለበት ነው ሲሉ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ምሁራን ተናገሩ።

በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህርት ዙሁራ መሐመድ እንደተናገሩት የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ሙያዊ ሃላፊነት ህዝቦችን ማግባባት ለሰላም እና ለአንድነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

“በፌደራልና በክልል ደረጃ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሀን የጥላቻ ንግግርን በማስወገድ ወደ ጋራ አስተሳሰብ እና ስምምነት መምጣት አለባቸው” ብለዋል፡፡

መገነኛ ብዙሀን ለህዝብና ለሀገር መወገን እንዳለባቸው የገለጹት መምርህቷ አንዳንድ የፌዴራል እና የክልል መገናኛ ብዙሃን ችግሮች በማባባስ ሙያዊ ሃላፊነት የጎደላቸውን ይዘቶች እያሰራጩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለአንድ ሕገ-መንግስት ለአንድ ሀገር እና ለህዝብ የሚሰሩ መገናኛ ብዙሀን በአላማና በሙያዊ ሃላፊነት ሊለያዩ እንደማይገባ ገልጽው በሙያ ደረጃ በማመን ሌላኛውን ማውገዝ ተገቢ እንዳልሆነና ሁሉም በመረጃ ሰጭነት በተዓማኒነት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

“በሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ህግና መመሪያ የማይሰሩ መገናኛ ብዙሀን  ሊጠየቁ ይገባል” የጥላቻ ንግግርን በማሰራጨት ህዝቦች ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጉ ሚዲያዎች በመለየት የብሮድካስት ባለስልጣን ሃላፊነቱ እንዲወጣ ጠቁመዋል።

“በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ያለውን የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ተጠቅመው ህዝቦችን በማቀራረብ እና ችግሮችን በማውጣት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ሊሰሩ ይገባል” ያሉት ደግሞ የዘርፉ ምሁር ጽጋቡ ሞትባይኖር ናቸው።

የአንዳንዶቹ መገናኛ ብዙሃን የይዘት አቀራረብ ሙያዊ ኃላፊነት የጎደለው መሆኑን ገልጸው “የመንግስት አቅጣጫ ብቻ በመከተል ከመንግስት ጋር መወገንም ተገቢ አይደለም” ብለዋል፡፡

“መገናኛ ብዙሀን ከመንግስት አጀንዳ እና አቅጣጫ ወጥተው ያሉቱን ችግሮች በመፈተሽ ህዝብና መንግስት በጋራ የሚፈቱበት እና ሀገራዊ አንድነት የሚጠናከርበት አሰራር ሊከተሉ ይገባል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ገብረጀወርግስ አብርሃ በበኩላቸው የሚታየውን ክፍተት መነሻ በማድረግ መገናኛ ብዙሃን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲገቡ የአቅምና የእውቀት ግንባታ እየተሰራ እንደሆነ ገለጸዋል።

“ባለስልጣኑ በአዋጅ መገናኛ ብዙሃንን የመቆጣጠርና ክፍተቶች ካሉ እንዲያሰተካክሉ በመደገፍ  ህጋዊ አሰራር ተከትለው እንዲሰሩ አቅጣጫን የመስጠት ስልጣን አለው” ብለዋል፡፡

በጥላቻ ንግግር እና በተቃርኖ የሚመጣ ለውጥና አንድነት የሚገነባ ሀገር እንደሌለ ዳሬክተሩ ገልጸው “መገናኛ ብዙሃኑ ለሀገር እና ህዝብ እሰራለሁ ብለው ከተቋቋሙለት አላማ አንጻር ሲታይ ወደዚህ ይገባሉ ብለን አናምንም” ብለዋል።

“ለሀገሪቱ እድገት እኩል ድርሻ አለኝ፣ ህብረተሰቡን እናገለግላለን ከሚሉ መገናኛ ብዙሀን  የጥላቻ ንግግር እና ተቃርኖ አይጠበቅም” በማለት አሁን የሚታዩ ክፍተቶች ህገ-ደንቡን ካለማወቅ የሚመነጭ ነው ብሎ ባለስልጣኑ እንደሚያምን ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ የሚዲያ አመራርና ባለሙያን የማብቃት፤ የመደገፍ እና የአቅም ግንባታ ስልጠና የመስጠት ስራ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም