የፀረ-ኤች አይቪ መድኃኒት የሚያቋርጡ ታካሚዎች ለከፋ የጤና እክልና ሞት መጋለጣቸው ተጠቆመ

61

አዳማ ጥር 4/2011 የፀረ-ኤች አይቪ መድኃኒት የሚያቋርጡ ታካሚዎች ለከፋ የጤና እክልና ሞት እየተጋለጡ መሆናቸው ተጠቆመ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  የሴቶች፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  አባላት የአዳማ ከተማ ጤና ጣቢያን የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያተኮረ የመስክ ምልከታ አድርጓል።

በዚህ ወቅት የአዳማ ከተማ ጤና ጣቢያ የኤች.አይቪ ኬዝ ማናጀር አቶ ግርማ መገርሳ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ጤና ጣቢያው ለአንድ ሺህ 568 የኤች አይቪ ህሙማን ነፃ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው።

በተቋሙ ተመላላሽ የፀረ ኤች አይቪ ህክምና በመከታተል ላይ ከሚገኙት መካከል 60ዎቹ ህፃናት ሲሆኑ ቀሪዎቹ አዋቂዎች ናቸው።

ጤና ጣቢያው ለነዚሁ ወገኖች የተሟላ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም ህሙማኑ በግንዛቤ ማነስ በእምነት ተቋማት ከበሽታው ተፈውሰናል በሚል  የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት እያቋረጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ጤናቸው በከፍተኛ ደረጃ ታውኮና ለጉዳት ተጋልጠው ወደ ጤና ጣቢያው እንደሚመለሱም ጠቁመዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ስምንት የኤች አይቪ ህሙማን መድኃኒት በማቋረጥ በደረሰባቸው የከፋ ጉዳት ለሞት መዳረጋቸውን ጠቅሰዋል።

"ችግሩን ለመከላከል የጤና ጣቢያው የኤች አይቪ ኬዝ ክትትል ባለሙያዎች መድኃኒት ለሚያቋርጡና የመድኃኒት አወሳሰድ ችግር ላለባቸው ህሙማን ቤት ለቤት ጭምር የምክር አገልግሎት ለመስጠት ቢሞክረም አጥጋቢ ለውጥ አልመጣም  "ብለዋል።

በተለይ መድኃኒት አቋርጠው የጠፉትን በስልክ ለማፈላለግ ጥረት ቢደረግም ተፈውሰናል ዳግመኛ እንዳትደውሉልን የሚል መልስ ስለሚሰጡ ችግር እንደሆነባቸውም አመልክተዋል።

በፀረ ኤች አይቪ ህክምና በሚያቋርጡት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት አሳሳቢ በመሆኑ የቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ እንደሚያሻም ጠቁመዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው በ2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በአዳማ ከተማ በተመረጡ የጤና ተቋማት ላይ የሚያደርጉትን የመስክ ምልከታ በቅርቡ ሲያጠናቅቁ ግብረመልስ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም