በጎንደርና በደቡባዊ ዞን የጥምቀት በዓል ያለጸጥታ ችግር እንዲከበር ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

866

ጎንደር /ማይጨው ጥር 4/2011 በጎንደር ከተማና በትግራይ ደቡባዊ ዞን የጥምቀት በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ዝግጅት  መደረጉ ተገለጸ፡፡

የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኦፊሰር ዋና ኢንስፔክተር አበበ አለባቸው  እንዳሉት በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስፈለጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በየክፍለ ከተማው ታቦቱን እንዲያጅቡ ተግባርና ኃላፊነት ተሰጥቷቸው በቤተክርስቲያን በኩል ተመርጠው የተደራጁ ወጣቶች መኖራቸው ጠቁመው ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

ጎንደርን ከሚያስጠሩና ከማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ የሆነውን የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የገለጹት ደግሞ  የከተማው ባህልና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ ናቸው፡፡

አንድ አብይ እና ሰባት ንኡሳን ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ያመለከቱት ኃላፊው ባህረ ጥምቀቱን ከማፅዳትና ውሃ ከመሙላት ጀምሮ ለሚመጡ እንግዶች መቀመጫ የሚሆን የሰገነት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የመብራትና የውሃ መቋረጥ እንዳይገጥም በከተማ አስተዳደሩ በኩል አስፈላጊው በጀት ተመድቦ ወደ ስራ ተግብቷል፡፡

በጎንደር  የፋሲል ክፍለ ከተማ ነዋሪው ወጣት ኤልያስ አበባው በበኩሉ በቀበሌያቸው የወጣት አደረጃጀት በመፍጠር በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከወዲሁ እቅድ አውጥተው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግሯል፡፡

ታቦታቱ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ተነስተው ወደ ጥምቀተ ባህሩ በህዝቡ ታጅበው በሰላም እስኪደርሱ ድረስ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ የሚከታተልና የሚያስተባብር ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጹዋል፡፡

የገብርኤል ክፍለ ከተማ ነዋሪው  ወጣት ደርበው ካሴ  በሰጠው አስተያየት ባለፉት ዓመታት ወጣቱ በጥምቀት በዓል ወቅት ፀጥታውን በማስጠበቅ በኩል ትልቅ ሚና እንደነበረው አስታውሷል፡፡

“በአደረጃጀት የታቀፈው እያንዳንዱ ወጣት ተግባርና ኃላፊነቱን የሚገልፅ የደረት ባጅ እየተዘጋጀ ነው “ያለው ወጣት ደርበው በጥምቀተ ባህሩ ላይም የፅዳት ስራ መጀመሩን ጠቁሟል፡፡

በኃይማኖታዊ በዓሉ ለመታደም ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚመጡ ምእመናንና እንግዶችን ወጣቱ የእንግዳ ተቀባይነት ባህሉን ጠብቆ ለማስተናገድ መዘጋጀቱን  የማራኪ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሲሳይ አማረ  ተናግሯል፡፡

በዓሉ የሰላም መገለጫ በመሆኑም ሁሉም የከተማዋ ወጣቶች ለሰላም ዘብ እንዲቆምም መልዕክቱን አስተላልፋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ ደቡባዊ ዞን የጥምቀት በዓልን በሰላም እንዲከበር ለማድረግ የዞኑ  ወጣቶች በበጎ ፈቃደኛነት የአካባቢያቸውን ፀጥታ እየጠበቁ መሆናቸውን ተገልጿል።

በተደራጀ መልኩ የጥበቃ ስራው እየሰሩ ያሉት በዞኑ የአላማጣ፡ ማይጨው፣መሆኒ እና የኮረም ከተሞች ወጣቶች ናቸው።

በከተሞቹ በዓሉን በሰላም እንዲከበር ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶች በጥበቃ ስራው መሰማራታቸውን የዞኑ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ኮማንደር ሐየሎም መቸ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶቹ የጦር መሳሪያ ዝውውርና አደገኛ ስለታም ቁሳቁሶችን መያዝን ጨምሮ ግጭቶችን በመቆጣጠር ህግና ስርዓት የማስከበር ስራ  እያከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የትራፊክ ፍሰት ስርዓቱን ጠበቆ እንዲሄድ የማድረግ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ኮማንደር ሐየሎም ጠቅሰዋል።

የአላማጣ ፀጥታ ማስከበር ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ሻምበል አማረ በበኩሉ በቅርቡ 162 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተደራጅተው በፀጥታ ማስከበር ስራ ከተሰማሩ ወዲህ በከተማው አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን ተናግሯል፡፡

ወጣቱ እንዳለው በከተማው የሚከበረውን የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲካሄድ ወንጀልን የመከላከል ተግባር እያከናወኑ ናቸው፡፡

ወጣቶቹ እስከ ሌሊቱ 8 ሰዓት የቅኝት ስራ፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና ስለታም ቁሳቁሶችን ተከታትሎ የመያዝ ፣ የሚከራዩ መኝታ ቤቶች ፍተሻና ክትትል ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

በመኾኒ ከተማ የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲካሄድ የ24 ሰዓታት የፀጥታ ጥበቃ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ በከተማው ፀጥታ ማስከበር ማህበር አባል  ወጣት ሃፍታሙ ገብረ ነው፡፡

” በፖሊስ አባላት የተሰጣቸው ስልጠናም የፀጥታ ማስከበሩ ህግን ተከትለን እንድንሰራ ረድቶናል ” ብሏል፡፡

በማይጨው ከተማ የጥምቀት በዓል ሰላማዊ ሆኖ  እንዲጠናቀቅ አካባቢያቸውን እየጠበቁ መሆናቸውን  በራሱ ፍላጎት በፀጥታ ማስከበር ስራ ማህበር የተደራጀው  ወጣት አያሌው ግርማይ ተናግሯል፡፡