የሱኑታ መስኖ ፕሮጀክት ወደ ስራ ባለመግባቱ ቅሬታ ፈጥሯል

1161

ሰመራ ጥር 4/2011 በአፋር ክልል እዋ ወረዳ የሚገኘው የሱኑታ መስኖ ፕሮጀክት ወደ ስራ ባለመግባቱ  ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ   አስተያየታቸውን የሰጡ ከፊል አርብቶ አደሮች ቅሬታቸውን ገለጹ።

ከከፊል አርብቶ አደሮቹ መካከል አቶ   መሀመድ ሜኤ ለኢዜአ እንዳሉት የአካባቢውን አርብቶ አደር ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ  በ2005 ዓ.ም. ተጠናቋል ።

ፕሮጀክቱ እስካሁን ወደ ስራ ባለመግባቱ  እስካሁን ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ተናግረዋል ።

“ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት የተገነባው ፕሮጀክት ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ህብረተሰቡ የሚጠብቀውን ጥቅም ሳያገኝ ቀርቷል” ያሉት ደግሞ ሌላው  ከፊል አርበቶ አደር አሊ ወዴ ናቸው ።

የአካባቢው ህብረተሰብ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በመስኖ እርሻ በማካሄድ  ለሰውና ለእስሳት የሚሆን የመጠጥ ውሀ እጥረቱን ለማቃለል የነበረው ተስፋ እውን ባለመሆኑ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

“ፕሮጀክቱን መሰረት በማድረግ ይካሄዳል በተባለው የመንደር ማሰባሰብ ትግበራ ላይ ህብረተሰቡ ጥርጣሬ እንዲያድርበት አድርጎታል” ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ስራ ባለመጀመሩ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የተገጠሙለት ማሽኖች በጸሐይና ንፋስ ብልሽት እየደረሰባቸው   መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ጠቁመዋል፡፡

ስለጉዳዩ የተጠየቁት የክልሉ እንስሳት፣ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ሁሴን በሰጡት ምላሽ የሱኑታ መስኖ ፕሮጀክት ለዘላቂ ልማት ግብ ማስፈጻሚያ በተገኘ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጥቶበት በ2005 ዓ.ም. መጠናቀቁን አረጋግጠዋል።

“ፕሮጀክቱ በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃ በመጠቀም 2ሺህ 400 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው ” ያሉት ኃላፊው አርብቶ አደሩን ከእንስሳት እርባታ በተጓዳን በእርሻ ልማት እንዲሳተፍ ታሰቦ መከናወኑን ተናግረዋል ።

ስራው በመከላከያ ኮንስትራክሽን አማካኝነት መከናወኑን ጠቁመው  “ፕሮጀክቱ በኃይል አቅርቦት በዲዛይንና ተያያዥ በሆኑ ችግሮች ምክንያት ወደ ስራ ሳይገባ ቆይቷል ” ብለዋል ።

ፕሮጀክቱን ሊመራ የሚችል የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር ወደ ስራ ለማስገባት ያልተቻለበት ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል ።

ከአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር መስሪያ ቤት ጋር በመተባበር ፕሮጀክቱ ያሉበትን የዲዛይንና ሌሎች ችግሮች በመፍታት እስከ መጪው ዓመት ባለው ጊዜ  ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

ከዲዛይን ማሻሻል በተጓዳኝ የተበላሹ መሳሪያዎች ጥገና፣ የውሀ መፍሰሻ ቦይ ዝርጋታ፣ የመሳሰሉ ስራዎች እንደሚከናወኑ አመላክተዋል ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ፕሮጀክቱ በአሁን ወቅት የ24 ሰዓት የኤሌክርትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲያገኝ በመደረጉ በተያዘው ዓመት 400 ሄክታር መሬት ለማልማት የመሬት ዝግጅት ተጀምሯል ።