በክረምቱ በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት ይጠበቃል

96
አዳማ ግንቦት 18/2010 ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የዘንድሮው የክረምት ወቅት በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር ዛሬ ይፋ ባደረገው ትንበያ አስታወቀ። ኤጀንሲው ትንበያውን ይፋ ያደረገው ከሁሉም ዘርፎች ለተወጣጡ ከ300 በላይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በተገኙበት በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነው ። የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለፁት ኤጀንሲው ባለፈው ወር የሰጠው የበልግ ወቅት ትንበያ በአመዛኙ ከእውነታው ጋር የተጣጣመና ውጤታማ ነበር ። በበልግ ወቅት ዋነኛ የዝናብ ተጠቃሚ የሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ ቆላማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን እንዳገኙ በጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል ። እንደ በልግ ወቅት ሁሉ የዘንድሮው የክረምት ወቅት ትንበያ እንደሚያመለክተው አብዛኛዎቹ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የአገራችን ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን እንደሚኖራቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በትንበያው መሰረት በሰሜን ምዕራብ አብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ የሚያገኙ ሲሆን የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም በሰሜን፣ ሰሜን ምስራቅ፣ ምስራቅና መካከለኛ አካባቢዎች በአብዛኛው ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል ። የደቡብ ከፍተኛ ቦታዎችና የሰሜን ሶማሌ አብዛኛው አካባቢዎች ወደ መደበኛ ያዘነበለና በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ሊኖራቸው እንደሚችል ዋና ዳይሬክተሩ ትንበያውን ዋቢ አድርገው ተናግረዋል ። የዘንድሮው የክረምት ወቅት የዝናብ አገባብ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከመደበኛው ጋር በተቀራረበ ጊዜ የሚጀምር ሲሆን በሰሜን ምዕራብ ግን በመጠኑ ዘግይቶ ሊጀምር ይችላል ተብሏል ። በአንጻሩ ዝናቡ በብዙ አካባቢዎች ከመደበኛው ጋር በተቀራረበ ሁኔታ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። በበልግ ወቅት ዝናብ በጠገበ መሬት ላይ በክረምት ወቅት ከሚጠበቀው መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ጋር ተዳምሮ በረባዳማና ወንዝ አጠገብ በሚገኙ አካባቢዎች ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ከወዲሁ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ኤጀንሲው አሳስቧል ። በኤጀንሲው የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ  ዳይሬክተር አቶ አሳምነው ተሾመ እንደገለፁት በዘንድሮው የክረምት ወቅት የሚጠበቀው የዝናብ መጠን መልካም አጋጣሚዎች ያሉትን ያህል በግብርናው፣ በኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ በተፋሰሶችና በጤናው ዘርፍ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር አስፈላጊው ዝግጅት ሊደረግ ይገባል ። የበልግ ወቅት ትንበያውን ውጤት ለመገምገምና የክረምት ወቅት ትንበያ ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተው በጋራ መክረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም