ለአካባቢያቸው ሰላም መጐልበት እንደሚሰሩ የተለያየ እምነት ተከታዮችና የሀገር ሽማግሌ ተናገሩ

663

ፍቼ ጥር 4/2011 በመካከላቸው ያለውን መቻቻልና መከባበር አጠናክረው ለአካባቢያቸው ሰላም መጐልበት እንደሚሰሩ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተለያየ እምነት ተከታዮችና የሀገር ሽማግሌ ተናገሩ፡፡

የኦርቶዶክስ ፣ የእስልምና፣ የኘሮቴስታንት እምናት ተከታዮች ፣ አባገዳና የሀገር ሽማግሌዎች በአካባቢቸውን ሰላም  ዙሪያ ዛሬ በፍቼ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች  በዞኑ ለረጅም ዘመናት የዘለቀውን የመቻቻል ባህል በማጠናከር የጥፋት ኃይሎችን አጀንዳ ለማክሸፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል የግራር ጃርሶ ወረዳ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መምሬ ደመቀ ወርቁ በበጐ ምግባር የታነፀ ዜጋ በማፍራት የተጀመረውን ለውጥ ለማጠናከር  እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በአካባቢያቸው የሚካሄዱ የሰላም፣ የልማትና የፀጥታ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በእምነታቸው መርህ መሰረት ህብረተሰቡን እንደሚያስተምሩ አመልክተዋል፡፡

የፍቼ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ተወካይ ፓስተር ሰለሞን ወርቁ በበኩላቸው  የህብረተሰቡ የቆዩ የመቻቻል ፣የመከባበርና አብሮ የመኖር ባህል በማጐልበት ለአካባቢያቸው ሰላም  ቅድሚያ በመስጠት እንደሚያስተምሩ ገልጸዋል፡፡

የእምነት እኩልነት በህገ መንግስት የተረጋገጠ በመሆኑ በመካከላቸው ልዩነትን በመፍጠር በአካባቢያቸው የሰላም ለማወክ የሚጥሩ ኃይሎችን ለህግ እንዲቀርቡ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡

በአካባቢያቸው የተለያየ እምነት ተከታዮችና  ብሔሮች ተቻችለውና ተጋግዘው  የኖሩበት አኩሪ ባህላዊ እሴት እንዳለ የተናገሩት ደግሞ የያያ ጉለሌ ወረዳ አባ ገዳ ታምሬ ቱሉ ናቸው፡፡ 

ይህንን  አኩሪ ባህላዊ እሴት ጠብቆ  ግጭትና አለመግባባቶችን በመፍታት ሰላምና  ልማትን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰው  እሳቸውም ያላቸውንም ተሰሚነት በመጠቀም ለዚህ በጎ ተግባር መቀጠል ቅድሚያ  ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

” የውይይት መድረኩ  መግባባትን በማጠናከር በሰላምና ልማት ዙሪያ የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንዲጠናከር ይረዳል “ያሉት በአካባቢው  ሽማግሌው የሆኑት አቶ ማሞ በላቸው ናቸው፡፡

ውይይቱ በተደራጀ መልኩ በቀጣይ መካሄድ እንዳለበትም ጠቁመው አስተዳደሩም ከህብረተሰቡ ለሚቀርቡለት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደር ሴቶች ማህበር ተወካይ ወይዘሮ ታደሉ ኃይሉ በበኩላቸው  የእምነት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ወጣቱን በመልካም ሥነ-ምግባር የመኮትኮት ኃላፊነት የሚወጡበት ታሪካዊ ወቅት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቱ ብሔሮችና የተለያዩ እምነት ተከታዮች ተከባብረውና ተቻችለው በመኖር ለአለም ህብረተሰብ ተምሳሌት መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ አስተዳደር ተወካይ አቶ ታደሰ ቦደና ናቸው፡፡

ይህንን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላተን  ነቅቶ መጠበቅና መከላከል ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በአካባቢው የሰላምና የፀሎት ኘሮግራም ለማወጅ እቅድ መዘጋጀቱም ተገልጿል ፡፡ 

በውይይቱ  ከዞኑ 13 ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያ እምነት ተከታዮችና  የሀገር ሽማግሌዎች ጨምሮ 25ዐ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡