በተቋማቸው ሰላማዊ የትምህርትን ስራ ለማሳካት እየሰሩ መሆናቸውን በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ገለጹ

1189

አምቦ ጥር 4/2011 በተቋማቸው አስተማማኝ  የሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማሩን ስራ ለማሳካት እየሰሩ መሆናቸውን በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ገለጹ፡፡ 

ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን ለማስቀጠል የዩኒቨርስቲው መምህራን የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፉ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

ዘወትር የመማር ማስተማር ሂደትን ከመጀመራቸው በፊት ለተማሪዎች ስለ ሠላም አስፈላጊነት ግንዛቤ በመስጠት ላይ መሆናቸውን መምህራኑ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት አስታውቀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው  የእንግሊዘኛ ትምህርትመምህር  ዳዊት ነገሪ እንደገለፁት መምህር የሁሉም ሙያ መሠረት እንደመሆኑ ሠላም በማስፈን ረገድም ፈር ቀዳጅ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

“ባሳለፍነው ወር መጀመሪያ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተከስቶ የነበረው የተማሪዎች የእርስ በእርስ አለመግባባት ጉዳት ሳያደርስ እልባት ያገኘው መምህራን የሠላም አምባሳደርነት ሚናቸውን በተግባር በመወጣታቸው ነው “ብለዋል፡፡ 

መምህራን በተማሪዎች መካከል በመግባት ሠላም የማውረድና የእርቅ መድረክ በማዘጋጀት ሆድና ጀርባ ሆነው የነበሩት ተማሪዎች እንዲታረቁ ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ  የግቢው ሠላም በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዳለ የገለጹት መምህሩ ለወደፊትም ተመሣሣይ ችግር እንዳይከሰት መምህራን ለተማሪዎቻቸው ስለ ሠላም አስፈላጊነት ግንዛቤ በመፍጠር ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል ።

በማህበራዊ ትምህርት ክፍል በኩል በግቢው ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የሁሉም ድርሻ ምን መሆን ያለበትን ጥናት መካሄዱን የገለፁት መምህር ዳዊት የጥናቱ ረቂቅ ሰነድ ከተጠናቀቀ በኋላ ለውይይት እንደሚቀርብ አስረድተዋል ።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን፣ የትምህርትና ስነ ባህሪይ ትምህርት ክፍል መምህር ቦንሣ ቱሉ በበኩላቸው መምህራን ግጭት ሲከሰት  ከሁሉም ተማሪ ጎን በመሆን በማርገብ ረገድ የሠላም አምባሳደርነት ሚናቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

“መምህራን ለራሳቸው ሳይሳሱ በተማሪዎች ግጭት መሃል በመግባት  የማረጋጋትና የመምከር እንዲሁም እንደ አባት የመገሰጽ ተግባርን ሲወጡ በመቆታቸው አሁን ላይ በተቋሙ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እየተተገበረ ይገኛል” ብለዋል፡፡

በቀጣይ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር መምህራን ለመረጃ ቅርብ በመሆን ሠላምን ለማደፍረስ የሚወጠኑ ማንኛውንም እኩይ ተግባራት ለማክሸፍ ቀድመው ምላሽ እንዲሰጡ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም አስታውቀዋል፡፡

በተቋሙ ውስጥ ባሉ ሁሉም የትምህርት ክፍሎች በኩልም ለተማሪዎች ስለ አንድነት፣ ሠላምና መቻቻል ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በማቀናጀት ውይይት መካሄዱን መምህር ቦንሣ አስረድተዋል ፡፡

በዩኒቨርሲቲው  የአራተኛ ዓመት የሲቪል ምህንድስና ተማሪ ስንታየሁ ባጫ በሰጠው አስተያየት መምህራን በትምህርት ክፍል ገብተው ስለ ሰላም አስፈላጊነት ሰፊ እውቀት እንዲጨብጡ እያገዟቸው መሆኑን ተናግሯል።

“እኛም ከእውቀት አባቶቻችን እንደቀሰምነው ሁሉ ከቤታችን የወጣንበት ዋነኛ ዓላማ ትምህርታችንን ከግብ ለማድረስ ሠላማችንን በመጠበቅ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እንጫወታለን ” ብሏል፡፡

በአምቦ ከተማ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ አያንሣ ፈዬራ በበኩላቸው የትምህርት ተቋማት ሠላም በሚደፈርስበት ጊዜ የሀገር ሽማግሌዎች በቀዳሚነት የማረጋጋት ስራ የማከናወን ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

መምህራን አሁን የያዙትን የሠላም አምባሳደርነት ተግባር ዘላቂነት እንዲኖረው ከጎናቸው በመቆም እንደሚደግፉም ገልጸዋል፡፡