የቀድሞው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ከሰተብርሃን 'የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ' ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ

99

አዲስ አበባ ጥር 4/2011 የቀድሞው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ 'የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ' ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው መሾማቸው ተገለጸ።

ቢግ ዊን ፊላንትሮፒ የአፍሪካ ባለራዕይ መሪዎች አጋር በማድረግ በአህጉሩ ልማት፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት፣ የሰለጠነ ሰው ልማት፣ ትምህርት ለምርታማነት እንዲውል እና በወጣቶች የስራ ዕድል ዙሪያ የሚሰራ ተቋም ነው።

ተቋሙ ይፋ እንዳደረገው ዶክተር ከሰተብርሃን ተቋሙ ከተመሰረተበት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር 2015 ጀምሮ ተቋሙን ሲመሩ የቆዩትን የቀድሞ የናይጄሪያ የጤና ሚኒስትር የነበሩትን ዶክተር ሙሃመድ አሊ ፔትን በመተካት ነው።

የተቋሙ ሊቀመንበር ጃሚ ኩፐር እንደገለጹት፤ ዶክተር ከሰተብርሃን የተቋሙን አላማ ማሳካት የሚችሉ ታማኝና ቁርጠኛ እንዲሁም የህጻናትን ህይወት የተሻለ ለማድረግና የወጣቶችን ዕድል ማስፋት የሚችሉ ናቸው።

ተቋሙ አጋር ባደረገው የኢትዮጵያ መንግስት ውስጥ ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸውን ያስታወሱት ሊቀመንበሯ፤ ለአገራቸውም ሆነ ለአህጉሩ የሚጠቅም አዎንታዊ ውጤት ያመጣሉ ተብሎ እንደታመነባቸው ገልጸዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ዶክተር ከሰተብርሃን በበኩላቸው ተቋሙን በኃላፊነት ሊቀላቀሉ የቻሉት የህዝባቸውን ህይወት ለመቀየር የሚያስችል አጀንዳ ቀርጸው ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በህጻናትና ወጣቶች ዙሪያ የሚሰራ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዶክተር ከሰተብርሃን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በህክምና የተመረቁ ሲሆን በኢትዮጵያ የተለያዩ ሆስፒታሎች በሙያቸው አገልግለዋል።

ከዚያም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥ ሚኒስቴር ዴኤታና ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል።

በአሁኑ ወቅት በአለም የጤና ድርጅት ውስጥ 'ሮልባክ ማላሪያ' በተሰኘ በወባ በሽታ መከላከል ላይ የሚሰራ ድርጅት ውስጥ ሃላፊ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም