የሚኒስትሮች ምክር ቤት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ለማቋቋም የቀረበው ረቂቅ አዋጅና በማዕድን ግብይት ረቂቅ አዋጅ ላይ ውሳኔ አሳለፈ

76

አዲስ አበባ ጥር 4/2011 61ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ያካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በማዕድን ግብይት ረቂቅ አዋጅ እና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

ምክር ቤቱ በኢፌዴሪ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ባደረገው ውይይት፤ ዜጎች በየደረጃው በሚካሄድ ነፃ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ በመረጧቸው ተወካዮች አማካኝነት ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ስልጣናቸውን በተግባር ማዋል ይገባቸዋል።

ለዚህም ነፃ የምርጫ አስፈጻሚ አካል አስፈላጊ በመሆኑና በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ለማጠናከር ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን ከማንኛውም አካል ነፃ አድርጎ በማደራጀት ፍትሃዊ፣ ተአማኒና ሰላማዊ ምርጫ ለማስፈጸም እንዲቻል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አዘጋጅቶ ባቀረበው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በስፋት ተወያይቶበታል።

ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ ላይ ተወያይቶ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል አዋጁን ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ለኢዜአ የላከው መግለጫ አመልክቷል።

በተመሳሳይ ምከር ቤቱ የሁሉንም አይነት ማዕድን ግብይት ለማስፋፋት፣ ሕጋዊ ስርአት ለማስያዝና ለመቆጣጠር በተዘጋጀው የማዕድን ግብይት ረቂቅ አዋጅ ተወያይቶ ማሻሻያዎችን በማከል ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም