የመማር ማስተማር ሥራው ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል የድርሻችንን እንወጣለን፡- በምስራቅ ወለጋ መምህራንና ተማሪዎች

86

ነቀምት ጥር 4/2011 በትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሥራው ሰላማዊና የተረጋጋ ሆኖ  እንዲጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ በምስራቅ ወለጋ ዞን መምህራንና ተማሪዎች ገለፁ ፡፡

በዋዩ ቱቃ ወረዳ የጉቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር እንዳለ ሙላቱ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ትምህርት ቤቶች ትውልድ በመልካም ስነ ምግባርና በእውቀት የሚቀረፁባቸው በመሆናቸው ተቋማቱ የሰላም ደሴት ማድረግ ያስፈልጋል ።

"ሰላም ከሌለ ተቋማቱ ዓላማቸውን ማሳካት አይችሉም " ያሉት መምህሩ በተቋማቱ ሰላምን ለማስፈን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

"ትምህርት ቤቶች ከፖለቲካ ነፃና ተማሪዎች ሕግና ደንብ አከብረው ትምህርታቸውን በመከታተል ውጤታማ ሊሆኑ ይገባል" ያሉት መምህሩ  ለተግበራዊነቱ ከመምህራን ብዙ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል ።

የነቀምቴ መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደረጀ በንቲ በበኩላቸው መምህራን የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ቀራጭ እንደመሆናቸው በትምህርት ቤቶች ሰላም የማስፈን ኃላፊነት እንደተጣለባቸው ተናግረዋል ።

በትምህርት ቤታቸው የመማር ማስተማሩ ስራ ሰላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።

"ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሥራን ለማረጋገጥ በየትምህርት ክፍሎች ለመምህራንና ለተማሪዎች ተከታታይ መስጠት ያስፈልጋል " ያሉት ደግሞ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ቦካ ኩምሣ ናቸው ፡፡

"በተቋሙ ስልጠናው እንዲሰጥና ተማሪዎች በቆይታቸው ራዕይ ሰንቀው እንዲወጡ ለማድረግ ኃላፊነታችንን እንወጣለን " ብለዋል ።

በዩኒቨርስቲው የምህንድስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ዲን አቶ ጉቱ ኦፍገኣ በበኩላቸው "መምህራን  ለተማሪዎች ዕውቀትና ክህሎት ከማስጨበጥ ጎን ለጎን በሥነ ምግባር ታንጸው እንዲወጡ  የማድረግ ኃላፊነት አለብን " ብለዋል ።

በተማሪዎች መካከል ግጭቶች እንዳይፈጠሩ በመከላከል መቻቻልና የተጠናከረ አንድነት እንዲኖር ማስተማር ይጠበቅብናል " ሲሉ ገልፀዋል ።

የቡርቃ ጃቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ መስቀሌ ሻንቆ "ተማሪዎች ባልተጨበጠ ወሬ በመሸበር ትምህርታችን ሳናቋርጥና ሕግና ደንብ  አክበረን በመማር የትምህርት ቤታችንን ሰላም ማረጋገጥ ይጠበቅብናል" ብላል ።

ትምህርት ማቋረጥ ተጎጂው ራሱ ተማሪ በመሆኑ የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማስተጓጎል ከሚፈልጉ ኃይሎች ራሱን መጠበቅ እንዳሚገባ ያመለከተው ደግሞ የነቀምቴ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ ጌታሁን ሽፈራው ነው።

ተማሪዎቹ  በትምህርት ቤቶቻቸው ለመልካም ስነ ምግባር በመገዛት የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ምስራቅ ወለጋን ጨምሮ በምዕራብ ኦሮሚያ በፀጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ማስተማር እየጀመሩ ስለመሆኑ ኢዜአ በተከታታይ ዘገቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም