የእንጦጦ ሐመረ ኖኀ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም ቤተ-መዘክር ለጎብኝዎች ክፍት ሆነ

673

አዲስ አበባ ጥር 4/2011 የእንጦጦ ሐመረ ኖኀ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም ቤተ-መዘክር ለጎብኝዎች ክፍት ሆነ።   

የቤተ-መዘክሩ የምረቃ ስነ ስርዓት  ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሄዷል።  

ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ የብራና መጻህፍት፣ የቤተ ክርስቲያን መገልገያ ዕቃዎችና የነገሥታት አልባሳትን የመሳሰሉ ቅርሶችም ለዕይታ ቀርበዋል።

የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ ጸባቴ አባ ወልደማሪያም አድማሱ እንደገለጹት፤ በቤተ-መዘክሩ ውስጥ የአጼ ሚሊኒክ፣ የባለቤታቸው ንግሥት ጣይቱ ፣ የልጃቸው ንግሥት ዘውዲቱና የአጼ ኃይለስላሴ መገልገያ ዕቃዎች ይገኛል።

የሰጎንና የዝሆን ጥርስም በቤተ መዘክሩ የሚገኙ መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው አትሌቶች በስጦታ ያበረከቱት ወርቆችና ብሮችም በቤተ-መዘክሩ ለዕይታ መቅረቡን አስረድተዋል።      

የቤተ-መዘክሩን ለእይታ ለመክፈት የህንጻ እድሳት መካናወኑን የገለጹት አባ ወልደማርያም፤ ዕድሳቱን ሳይጨምር 600 ሺህ ብር ወጪ መደረጉን  አብራርተዋል።   

ቤተ-መዘክሩ በርካታ ጠቃሚ ጥንታዊ ቅርሶችን የያዘ በመሆኑ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ አካላትም ግብዓት አንደሚሆን ጠቁመዋል።

”ቤተ መዘክር ትምህርት ቤት ነው” ያሉት አባ ወልደማርያም፤ ትውልዱ የአባቶችን አሻራ ሳይረሳ ነገን እንዲሻገር የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም መጥቶ እንዲጎበኝም ጥሪ አቅርበዋል። 

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ተወካይ ወይዘሮ ማሚቱ ይልማ በበኩላቸው ቀደምት አባቶች ለዘመናት ተንከባክበው ያቆዩትን ቅርስ አሁን ያለው ትውልድ አጥንቶ፣ ተንከባክቦና ጠብቆ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለበት ብለዋል።     

በተለይም ወጣቱ ትውልድ ባህሉን አውቆና ትኩረት ሰጥቶ ሙዚየሞች በጥራትና በብዛት እንዲስፋፉ፤ ያሉትም የሚፈለገውን አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ይኖርበታል ሲሉም ተደምጠዋል። 

ስለ ሙዚየሞች የተደራጀ መረጃ የሚሰጡ ሰነዶችን ወደ ቱሪስቶችና ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚያሻም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በገዳሙ የተገነባው ቤተ መዘክር ቅርሶችን ጠብቆና አቆይቶ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚደረገውን ጥረት በጉልህ እንደሚያግዝም ገልጸው፤ የቤተ መዘክሮች መጠናከርና መስፋፋት ቅርሶችን ከአደጋ ከመጠበቁም በላይ ለአገሪቷ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት የጎላ አስተዋጽኦ ያለው ነው ብለዋል።

በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለቤተ መዘክር ልማት ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታም በገዳሙ እንደዚህ ዓይነት ታራካዊ ቅርሶችን የያዘ ቤተ-መዘክር መከፈቱ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ ወጣቱ ታሪኩንና ማንነቱን እንዲገነዘብ በማድረግ በኩል የላቀ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል። 

ቅርሶችን በአግባቡ ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባ ያሳሰቡት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይ ዘመናዊ የቅርስ አያያዝ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ለዚህም ባለሥልጣኑ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ሲሉም አረጋግጠዋል።   

”በቤተ -መዘክሩ ከአገር ውስጥም ከውጭ በሚመጡ ጎብኝዎችና ቱሪስቶች ለማስጎብኘት የሚቻለውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን” ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ናቸው።  

በዕለቱ በገዳሙ ለሚገነባው የምዕመናን ሱባኤ መጠለያ ግንባታም በብጹዕ አቡነ ማትያስ አማካኝነት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጧል።  

በገዳሙ ለጎብኝዎች ክፍት የሆነው ቤተ-መዘክር በአዲስ አበባ ሰባተኛው ነው።      

ገዳሙ ከተቆረቆረ 1 ሺህ 450  ዓመት የሞላው ሲሆን አባ ሊባኖስ የተባሉ ሮማዊ ጻዲቅ እንደቆረቆሩት ከገዳሙ አስተዳዳሪዎች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።