በአጋሮ ከተማ አምስት የመድኃኒት መሸጫ መደብሮች ታገዱ

77

ጅማ  ጥር4/52011 የአጋሮ ከተማ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት በህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል ያላቸውን አምስት መድኃኒት መሸጫ መደብሮች ማገዱን አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሃፊዝ ጀማል ለኢዜአ ንደገለጹት የመድኃኒት መደብሮቹ ላይ እገዳው የተጣለው በገበያ ውስጥ የሚዘዋወሩ ህገ-ወጥ መድኃኒቶችን ለማስቆም እየተደረገ ባለው ቁጥጥር ነው።

"የመድኃኒት መደብሮቹ ያልተፈቀደ መድኃኒት ይዘው በመገኘታቸው፣ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች ለገበያ በማቅረባቸው፣ ከመድኃኒት ጋር  የመዋቢያ ምርቶችን ሲሸጡና  የመድኃኒት አያያዛቸው ደካማ መሆኑ ስለተደረሰበት እገዳ ተጥሎባቸዋል" ብለዋል ።

በመደብሮቹ ላይ እንደየ ጥፋታቸው ከ 20 ቀን እስከ አምስት ወር የሚደርስ የአገልግሎት እገዳ የተጣለባቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

ፈዋሽ ያልሆኑ ህገ-ወጥ መድኃኒቶች በገበያ ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት ኃላፊው ህብረሰተሰቡ መድኃኒቶችን ሲገዛም ሆነ ሲጠቀም የህክምና ባለሙያዎች እያማከረ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ህብረተሰቡ ህገ-ወጥ መድኃኒቶች ሲያጋጥሙት ለመድኃኒት ተቆጣጣሪዎችና ለጸጥታ አካላት መረጃ በመስጠት እንዲተባበር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም