የትምህርት ተቋማትን ከፖለቲካ ተጽእኖ ማላቀቅ ይገባል-ፕሮፈሰር ጣሰው ወልደሃና

75

አዲስ አበባ ጥር 4/2011 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከፖለቲካ ተጽእኖ በማላቀቅ በሰላም አብሮ የመኖር ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፈሰር ጣሰው ወልደሃና ተናገሩ።

ዩኒቨርሲቲው ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ''ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሰላም'' በሚል ዛሬ መክረዋል።

ፕሮፌሰር ጣሰው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የሰላም አብሮ የመኖር ባህልን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማሳደግ "ተማሪዎችን ከፖለቲካ እንቅስቃሴና ፉክክር ነጻ ማድረግ ይገባል"።

ባለፉት ዓመታት ሰላም ላይ ትኩረት ተደርጎ ባለመሰራቱ ተማሪዎች በዘር የመከፋፈልና እርስ በእርስ ያለመታማመን ችግሮች አጋጥሟቸዋል።

ይህም በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭትና ሁከትን በመቀስቀስ የመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ያመጣው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ተማሪዎችና መምህራን በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚያደርጉት ፉክክርና አንዳንድ ድርጅቶችም የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውን ያለገደብ በተቋማቱ ማራመዳቸው የተማሪዎችን አብሮነት እንደሸረሸረውም ነው ፕሮፌሰሩ ያብራሩት።

የዩኒቨርሲቲዎች ዋነኛ ተግባር ማስተማርና መመራመር መሆኑን አጽንዎት ሊሰጡት እንደሚገባም አመልክተዋል።

እንደ ፕሮፈሰሩ ገለጻ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ስድስት ወራት በተጽእኖ የሚካሄዱ የፖለቲካ አሰራሮችን በማጽዳትና የፖለቲካ ሃሳቦችን በነጻ የሚያራምዱበት የጋራ መድረክ በማዘጋጀት የተሻለ ሰላም ማምጣት ችሏል።

ዩኒቨርሲቲው በሰላም ዙሪያ የሚመራመርና ሃሰቦችን የሚያፈልቅ አስር አባላት ያሉት ቡድን አዋቅሮ በተቋሙ ቀጣይነተ ያለው ሰላም ለማምጣት እየሰራ ነውም ብለዋል።

ለቡድኑም አንድ ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀዋል።

ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ይህንን ተሞክሮ በማስፋት ለአገር ሰላምና ለአብሮነት የሚያደርጉትን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸውም ተመላክቷል።

በመድረኩ "'ሰላምና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት" በሚል ጽሁፍ ያቀረቡት በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ በበኩላቸው ሰላምን ለማስፈን ተቋማቱን ከፖለቲካ ተፅእኖ ነጻ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል።

በተለይ በተቋማቱ የሰላም እጦት መንግስትና ምሁራን በሰላም ላይ ያልተገበሯቸው በርካታ ተግባራት ለመኖራቸው ዋቢ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያዊ አብሮነትን ያካተተ መርሃ ግብር በመቅረጽ፤ በጎሳና በዘር የተከፋፈለውን የምደባ ስርዓት በመከለስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፌዴራል ተቋማት መሆናቸውን ማጉላትና የተማሪዎች ህብረትን ከፖለቲካ የጸዱ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ምሁራንም የግጭት አራጋቢዎች ከመሆንና የስራ መርሃ ግብራቸውን በአግባቡ ካለመወጣት ተቆጥበው ትውልድ የመቅረጽ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ  መኮንን እንዳሉት ምሁራን ''ለሀገሩ ቀና የሆነ ዜጋንና ስለ አገሩ ሰላምና ዲሞክራሲ የሚተጋ ዜጋን የማፍራት ሃላፊነት አለባቸው''።

በተለይ ምሁራን አገሪቷ አሁን ከገጠማት የሰላም እጦት ለመውጣት ሙያዊና የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

አንድ ቀን በሚቆየው የምከክር መድረኩ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተወከሉ መምህራን፣ የተማሪዎች መማክርት፣ የሰላም መልዕክተኞችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም