በኢትዮ-ቴሌኮም የኔትዎርክ ጥራት መጓደል ምክንያት ሥራችን እየተበደለ ነው….የአምቦ ከተማና አካባቢዋ ደንበኞች

1786

አምቦ ግንቦት 18/2010 በኢትዮ-ቴሌኮም የኔትዎርክ ጥራት መጓደል ምክንያት ሥራችን እየተበደለ ነው ሲሉ የአምቦ ከተማና አካባቢዋ ደንበኞች ቅሬታቸውን አሰሙ ።

በኢትዮ-ቴሌኮም የምዕራብ አዲስ አበባ ዞን በበኩሉ “የኔትወርክ መቆራረጥና ተያያዥ ችግሮች ከኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መጥፋት ጋር የሚመነጩ ናቸው” ሲል፤የአምቦ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም የቀረበበትን ቅሬታ አምኖ ተቀብሏል ።

የአምቦ ከተማና አካባቢዋ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ትናንት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከድርጅቱ ጋር ባደረጉት ውይይት የኔትዎርክ መቆራረጥ ስራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑና ለኪሳራ እንዲጋለጡ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል ።

ኔትዎርክ ጥራት መጓደል በሞባይል ተጠቃሚዎች፣ በኢንተርኔት ካፌ፣ በኮሚኒኬሽን ስራና በትምህርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን በውይይቱ  በስፋት ተነስቷል ።

የኢንተርኔት ካፌ ባለቤት ወይዘሪት አልማዝ አለሙ በሰጡት አስተያየት የኢንተርኔት መቆራረጥና ብልሽት ሲያጋጥማቸው በ994 ለማስመዝገብ ቢደውሉም ብዙ ጊዜ ስልኩ እንደማይነሳ ነው የገለጹት ።

“አንዳንድ ጊዜ ቢነሳ እንኳን ብልሽቱ ከመመዝገብ ባለፈ ፈጣን ምላሽ ስለማይሰጠን በስራችን ላይ እንቅፋት እየፈጠረና ለኪሳራ እየዳረገን ነው” ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል።

በኔትወርክ መቆራረጥ ምክንያት ባንኩ ለደንበኞች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአምቦ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ  አቶ ጋዲሳ ባይሳ ናቸው፡፡

ባንኩ ለደንበኞቹ ጥራትና ፍጥነት ያለው አገልግሎት ለመስጠትና አዲስ ደንበኞችን ለማፍራት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የኔትወርክ መቆራረጥ ተጽዕኖ በማሳደር ደንበኞቻቸው እንዲጉላሉ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል ።

የሜታ ወልቅቴ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በቀለ ጉተማ በበኩላቸው በወረዳቸው የመደበኛ ስልክ አገልግሎት ባለመኖሩ ከዞን የሥራ አመራሮች ጋር የሚገናኙት በተንቀሳቃሽ ስልክ ብቻ ነው፡፡

ተንቀሳቃሽ ስልኩ በኔትዎርክ ምክንያት ሲቆራረጥ መልዕክት በወቅቱ ስለማይደርሳቸው በትምህርት ሥራቸው ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

“ኢትዮ-ቴሌኮም የደንበኖቹን ችግር ተገንዝቦ በአፋጣኝ ለችግሮቹ መፍትሄ  መስጠት ይኖርበታል” ብለዋል፡፡

በኢትዮ – ቴሌኮም የምዕራብ አዲስ አበባ ዞን ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዬ ለማ በውይይቱ ላይ በሰጡት ምላሽ ደንበኞች ያነሱትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመፍታት ድርጅቱ  እየሰራ ቢሆንም ለሞባይል ኔትወርክ መስተጓጎል ዋናው ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የተጠቀሚዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ አገልግሎት በፍጥነትና በጥራት መስጠት የሚያስችል የማስፋፊያ ግንባታ በአምቦ ከተማ መከናወኑንም አክለው ገልፀዋል ።

በዘላቂነት ችግሩን ለማስወገድ በቀጣይ አምቦ ከተማ ውስጥ የኔትዎርክ ማዕከል ለመገንባት የከተማዋን አስተዳደር የግንባታ ቦታ ጠይቀው መልሱን እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የአምቦ ከተማ ኤሌክትሪክ  ኃይል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሽታዬ በኢትዮ-ቴሌኮም የተነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑን አምነዋል።

በመስመር ማርጀት የሚከሰት የኃይል መቆራረጥ መኖሩንና የማከፋፈያ ጣቢያው ከከተማ ውጪ መሆን የኃይል መቆራረጥም ሆን ብልሽት ሲያጋጥም ተሎ አውቆ ለማስተካከል እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል ።

የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚረዱ እርምጃዎች ለመውሰድ በቀጣይ በመስሪያ ቤታቸው በኩል የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።