የትምህርት ተቋማትን ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ጥራቱንም ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

908

ነገሌ ጥር 4/2011 መንግስት የትምህርት ተቋማትን ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ጥራቱንም ለማሻሻል ከትምህርት ስራ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ እንደሆነ ትምህርት ሚኒስትር አስታወቀ

የትምህርት ሚኒስቴር በጉጂ ዞን ቦሬ ከተማ ለሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጎል ፡፡

የተደረገው ድጋፍ  ለትምህርት ቤቶቹ  12 ኮምፒውተሮችና 500 መጽሐፍት እንዲሁም  ለ150 ተማሪዎች ደግሞ የደንብ ልብስ ፣ ደብተርና እስኪርብቶ ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር  መሀመድ አሊ  በከተማው በመገኘት 300ሺህ ብር የሚገመተው ይህንኑ ድጋፍ ትናንት ለጉጂ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አስረክበዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው በዚህ ወቅት  በተወለዱበትና በተማሩበት ጉጂ ዞን የነበረውን የመምህራን ትምህርት አሰጣጥ ፣ የተማሪዎች መልካም ስነ ምግባርና የወላጆችን ምክርና ድጋፍ አዎንታዊ ጎን አስታውሰዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወላጆችና መምህራን ቁጥጥርና ክትትል ማነስ በተማሪዎች ግድየለሽነትና መኮራረጅ የትምህርት ጥራት እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ጥራቱን ለማሻሻል ባለሀብቱ በድጋፍ ፣ መምህራን በክትትልና ቁጥጥር ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በጥሩ ስነ ምግባር በማነጽና የስራ ጫና በመቀነስ የየድርሻቸውን ወስደው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ተማረዎችም ትምህርት ሲጨርሱ ካሰቡበት ለመድረስና የወደፊት እቅዳቸውን ለማሳካት ሰዓት ማክበር ፣ታዛዥ መሆን ፣ ማጥናትና ስነ ምግባራቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ አሳስበዋል፡፡

 ” የዛሬ ተማሪዎች የነገ ኢንጂነር ፣ ዶክተር ሳይንስቲስትና የሀገር መሪ ለመሆንና ከድህነት ለመውጣት  መልፋት  ፣  መስራት ፣ ማጥናት ችግርን በትእግትስና በተስፋ ማለፍን ይጠይቃል” ብለዋል፡፡  

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት መንግስት የትምህርት ተቋማትን ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን ጥራቱንም ለማሻሻል ከትምህርት ስራ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ ነው፡፡

የትምህርት ስራ በመንግስት ብቻ  የሚያልቅ ባለመሆኑ አርብቶ አደርና አርሶ አደር እስከ ትምህርት ሚኒስትር ያለ ባለድርሻ ሁሉ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የጉጂ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ታደሰ  በበኩላቸው ” የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የውስጥ ድርጅቶችን በማሟላት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከትምህርት ስራ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጃራ በትምህርት አሰጣጥ ሞዴል የሆኑ 400 ትምህርት ቤቶች መመረጣቸውን ገልጸው የትምህርት አሰጣጡን ለማሻሻል በቅርቡ የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የቦሬ ከተማ ነዋሪ  መምህር ዮናስ ጬና ለተበረከተው ምስጋና አቅርበው በመምህርነት ሙያቸው ያላቸውን እውቀት በማካፈል የድርሻችውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ ተማሪ ሰሊ በራቆ በሚኒስትር ዴኤታው የተላለፈው መልዕክት አስተማሪና በርትቶ በመስራት የወደፊት እቅዱን ለማሳከት እንደሚጠቅመው ተናግሯል፡፡