ፍርድ ቤቱ በሰብአዊ መብት ጥሰት የተያዙ 33 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው ለአራት ተከፍሎ እንዲታይ ወሰነ

88

አዲስ አበባ ጥር 4/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነጎሕ አፅብሐ መዝገብ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተያዙ 33 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው ለአራት ተከፍሎ እንዲታይ ወሰነ።

በሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በተያዙ የቀድሞው የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ሠራተኞች ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ  የምርመራ ጊዜ ለመፍቀድ ከአራት ቀናት በላይ ክርክር ሲካሄድ ቆይቷል። 

በዚህ መዝገብ የቀረቡት ተጠርጣሪዎች በአራት ቦታ እንዲከፈሉ የተደረገው የፍትሕ ስርአቱን ለማፋጠን ሲባል መሆኑን ፍርድ ቤቱ ትላንት ባዋለው 10ኛ ወንጀል ችሎት ላይ ገልጿል።

ፖሊስ በነዚሁ ተጠርጣሪዎች ላይ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገው የጠየቀ ሲሆን በአራት መዝገብ ከፋፍሎ በማደራጀት እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ከ10 እስከ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዶለታል።

በተለያዮ ግለሠቦች ላይ የሠብዓዊ መብት ጥሠት በማድረስ፣ በማሠር፣ በማሠቃየት፣ በመደብደብና ወንዶችን በማኮላሸት መጠርጠራቸው ይታወቃል።

ፖሊስ በዚህ ወቅት በተደረገው ክርክር ላይ ለፍርድ ቤቱ እንዳቀረበው በተጠርጣሪዎች ላይ መረጃ የማሠብሠብ ስራዬን ባለማጠናቀቄ ተጨማሪ ቀን ያስፈልገኛል ብሏል።

የተጠርጣሪ ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ የምርመራ ስራውን በሚገባና እያንዳንዱ ተጠርጣሪ በለየ መልኩ እያቀረበ ባለመሆኑ የጊዜ ቀጠሮ ውድቅ መሆን አለበት ሲሉ ተከራክረዋል።          

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ቀረኝ ያለውን ስራ አጠናቆ ለጥር 10፣13፣15 እና 17 እያንዳንዱን መዝገብ እንዲያቀርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም