የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በሀዋሳ መምህራን ገለጹ

151

ሀዋሳ ጥር 4/2011 የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደሚጥሩ በሀዋሳ ከተማ መምህራን ገለፁ።

በሀዋሳ  የታቦር ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህርት መስታወት ጸጋዬ  ለኢዜአ እንደገለፁት የሰላም መኖር ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ሀገር አስፈላጊና መሰረታዊ ነገር ነው ።

“ያለሰላም መማርም ሆነ መስራት አይታሰብም ” ያሉት መምህርቷ ተማሪዎችን በስነ- ምግባር መቅረፅም ሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ማስፈን የመምሀራን ትልቁ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል ።

በትምህርት ጥራትና በመምህራን ጥቅማ ጥቅም ዙሪያ ትምህርት ቤታቸውን ወክለው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየታቸውን አስታውሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መምህር የሰላም አምባሳደር ነው ያሉትን ቃል በተግባር ለማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል ።

መምህሩ የአምባሳደርነት ሚናውን መወጣት የሚችለው መልካም ስነ-ምግባር ያለው በዕውቀት የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ጥሩ ዘር በመዝራት መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል።

ሌላው መምህርና የሀዋሳ ከተማ መሰረታዊ መምህራን ማህበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገረሱ ሀንሴቦ በበኩላቸው መምህር ያላስተማረውና የማያገኘው የህብረተሰብ ክፍል እንደሌለ ተናግረዋል ።

“በግንኙነቱም መደበኛውን ትምህርት ብቻ ሳይሆን ስለሀገር ሰላምና አንድነት ጭምር ያስተምራል” ብለዋል ።

በተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነትና ተሰሚነት ከሌላው ጋር ሲነጻጸር ላቅ ያለ በመሆኑ በሁሉም መስክ አምባሳደር ሆኖ ማገልገል እንደሚችል ተናግረዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት  ለመምህር የተሰጠው የሰላም አምባሳደር የሚለው ስያሜ ተገቢ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የስርዓተ ጾታ ተጠሪ ወይዘሮ ጤናዬ ታደሰ ናቸው፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል ጳውሎስ  “መምህራን ከተማሪዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ሰላምን ከመፍጠር አንጻር በትኩረት መስራት አለብን” ብለዋል ።

ማህበሩ  የመማር ማስተማር ስራው ሰላማዊ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ያመለከቱት  አቶ አማኑኤል  ከክልሉ ትምህርት ቢሮና ከሌሎች አካላት ጋር በመነጋገር የሰላም ኮንፈረንስ ለማካሄድ ማቀዳቸውንም ጠቁመዋል።