በተማሪዎች ስብእና ግንባታ ላይ ገንቢ ሚና እንደሚጫወቱ መምህራን ገለጹ

174

ጎባ ጥር 4/2011 ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የተላበሳ ስብእና እንዲጎናፀፉ ለማስቻል ገንቢ ሚና እንደሚጫወቱ በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲና በጎባ ባቱ መሰናዶ ትምህርት ቤት አስተያየታቸውን የሰጡ መምህራን ገለጹ፡፡

መምህራኑ ለኢዜአ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በየደረጃው ከሚገኙ መምህራን ጋር ያደረጉት ውይይት የመምህራንን ደረጃ የሚመጥንና ለከፍተኛ ኃላፊነት የሚያነሳሳ መድረክ ነበር፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ  የህግ ትምህርት ቤት ዲንና መምህር ሰለሞን ግርማ በምክንያት የሚያምንና ጥያቄውን ሁሉ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚያቀርብ ዜጋ ለማፍራት በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የዩኒቨርስቲው የህግ  ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፍ ሀሳብ ከሚማሩበት ተጓዳኝ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተቋሙ  በፍርድ ቤቶች በከፈታቸው ነፃ የህግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት እየተገኙ አገልግሎት እንደሚሰጡ አመልክተዋል፡፡

በዚህም ተማሪዎች በቆይታቸው በሚሰጡት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትምህርታቸውን ጨርሰው ከህብረተሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ ከተማሩት ሙያ ጋር የሚመጣጠን እውቀትና ስነ-ምግባር ባለቤት እንዲሆኑ የሚያግዛቸው መሆኑን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሲቪክስና ስነ ዜጋ ትምህርት ክፍል መምህር ተስፋዬ ዘውዴ በበኩላቸው  ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የተላበሰ ስብእና ተጎናጽፈው እንዲወጡ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መምህሩ እንዳሉት በተለይ በዩኒቨርሲቲው የተቋቋመው የስነ ዜጋና ስነ ትምህርት ክበብ ተማሪዎች የተለያየ ሀሳብን በዴሞክራሲያዊ አግባብ በማንሳት የመወያየት  ዝንባሌ እንዲያዳበሩ ያደርጋል፡፡

የሀሳብ ልዩነቶችን በዴሞክራሲዊ አግባብ  የማስተናገድ እሳቤን ከወዲሁ እንዲያጎለብቱ  ይረዳል፡፡

ተማሪዎች ለትምህርታቸው ቅድሚያ በመስጠት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ቀጣይነት ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲኖር ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክትም አመልክተዋል፡፡   

መንግስት የትምህርት ጥራትና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት የትምህርት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ በየደረጃው ከሚገኙ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ግብዓት እየሰበሰባ መሆኑ ለትምህርት ሴክተሩ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሳይ የተናገሩት ደግሞ የጎባ መሰናዶ ትምህርት ቤት መምህር  ግርማ ታምራት ናቸው ፡፡

“በየደረጃው የምንገኝ መምህራንም በየትምህርት ቤታችን ውጤታማ የሆነ ሰላማዊ የመማር ማሰተማሩን ስራ በማጠናከር የሰላም አምባሰደርነታችንን ለመወጣት ቁርጠኛ ነን “ብሏል፡፡

ሌላው ትምህርት ቤቱ  መምህር ሀብታሙ ጎንፋ በሰጡት አስተያየት   በትምህርት ቤታቸው መምህራን ተማሪዎቻቸውን በተለያዩ ክበባት ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም  እርሰ በራሳቸው በሚያስተላልፉት መልዕክት ከትምህርታቸው በተጓዳኝ ግብረገብነትን በመላበስ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆኑ ገንቢ ሚና ለመጫወት የድርሻቸው እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

መንግስትም መምህራን የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን በማፍራት በኩል እያደረጉ የሚገኘው ተግባር ወጤታማ እንዲሆን ከኑሮ ውድነትና ከትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት ጋር በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎችን በመለየት ደረጃ በደረጃ መፍታት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በየደረጃው ከሚገኙ  መምህራን ጋር ባደረጉት ውይይት ለተነሱት ሁሉን አቀፍ ጥያቄዎች በተሰጠው ምላሽ መርካታቸውንና ተግተው እንዲሰሩ  እንዳነሳሳቸውም ገልጸዋል፡፡