የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ፕሮጀክት እየተካሄደ ነው

294

አሶሳ ጥር 4/2011 የሃገሪቱን እንስሳትና ዓሣ ሃብት በሚገባ ለማልማት የሚያግዝ ፕሮጀክት በክልሎች እየተካሄደ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በፕሮጀክቱ እንቅስቃሴ ዙሪያ የተዘጋጀ አውደ ጥናት በአሶሳ ከተማ ተካሄዷል፡፡

በሚኒስቴሩ የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ ዶክተር ቶማስ ቸርነት በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የሀገሪቱን እንስሳትና ዓሳ ሃብት ለማልማት አዲስ ፕሮጀክት ተዘጋጅቶ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡

“በስድስት ክልሎች በሚገኙ ስምንት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ይኸው ፕሮጀክት አራት ቢሊዮን 600 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል” ብለዋል፡፡

ከዓለም ባንክ በተገኘ የረጅም ጊዜ ብድር የሚከናወነው ፕሮጀክቱ ለስድስት ዓመታት የሚቆይ ነው፡፡

እንደ አስተባባሪው ገለጻ ፕሮጀክቱ በወተት፣ ዓሣ፣ ዶሮ እርባታ እና ቀይ ሥጋ ልማት ላይ የተኩራል፤ ዝርያን ማሻሻል፣ መኖን በብዛት ማልማት፣ በሽታ መከላከልና ገበያን ማስፋት ደግሞ ዘርፉን ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው፡፡

ከፕሮጀክቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የጥናትና ምርምር አቅም ማዳበርና አዳዲስ የስልጠና ማዕከላትን እንደሚገነቡ አስረድተዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት አገራዊ ድርሻ ያለው የትግበራ አደረጃጀት መዋቀሩን ያመለከቱት ዶክተር ቶማስ ” ባለፉት ሰባት ወራት አፈጻጸሙ በሚፈለገው ልክ አይደለም” ብለዋል፡፡

ከፌደራል እስከ ክልሎች ፕሮጀክቱን የሚያስፈጽሙ ተቋማት ያጋጠማቸው የአደረጃጀትና የአመራር መቀያየር  አፈጻጸሙ በሚፈለገው ልክ እንዳይሄድ ያደረግ ምክንያት መሆኑን ተጠቅሷል፡፡

ለተያዘው የበጀት ዓመት ከተመደበው 364 ሚሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን ሥራ ላይ የዋለው ከ127 ሚሊዮን ብር መሆኑን አስተባባሪው አመልክተዋል፡፡

” ብድርን በአግባቡ ካልተጠቀምን በሃገር ላይ የሚያሳድረው የእዳ ጫና ከፍተኛ ነው፤ በጀትን በአግባቡ ተጠቅሞ የህብረተሰቡ ህይወት ለመለወጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ብለዋል፡፡

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ ፕሮጀክቱ የክልሉን ሃብት ለማልማት ወሳኝ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው አውደ ጥናት ከ30 የሚበልጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡