የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በ184 የፖሊስ አባላቱ ላይ እርምጃ ወስዷል

141

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 ከተቋሙ ተልኮ በተፃራሪ በወንጀል ድርጊት የተሳተፉና የስነ-ምግባር ችግር ያለባቸውን 184 የፖሊስ አባላትን ከሰራዊቱ ማሰናበቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ፡፡

ኮሚሽኑ በአገር አቀፍ ብሎም በከተማችን  ተግባራዊ የሆነውን ለውጥ ተከትሎ ከዚህ ቀደም በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማስተካከል ለከተማችን የሚመጥን ፖሊሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ልዩ ልዩ የለውጥና የመልሶ ማደራጀት ወይም የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አመላክቷል፡፡

ኮሚሽኑ ከህብረተሰቡ የተሰጡ ጥቆማዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የደረሱትን መረጃዎች መነሻ በማድረግ መላው የፖሊስ አባላትን ያሳተፈ ግምገማ ከማእከል እስከ ፖሊስ ጣቢያ ባለው መዋቅር ድረስ መድረጉንም ገልጿል።

በሰራው የማጥራት ስራም ከኮሚሽኑ ተልዕኮ ተፃራሪ በመሆን በልዩ ልዩ ከባድ ወንጀል ላይ የተሳተፉ እንዲሁም ከፖሊሳዊ ስነ-ምግባር ውጭ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 184 የፖሊስ አባላት ከሰራዊቱ እንዲሰናበቱ አድርጓል፡፡

በልዩ ልዩ የወንጀል ድርጊት ውስጥ ገብተው የተገኙ የፖሊስ አባለት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም ኮሚሽኑ ከላካው መግለጫ መረዳት ተችሏል፡፡

የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና ተቋሙ ህዝብና መንግስት የጣሉበት ከፍተኛ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ቀጣይነት ያለው የማጥራት ስራዎችን አጠናክሮ  የሚቀጥል መሆኑን ገልፆ፤ በቅርብ ጊዜ መላውን አባልና አመራር ያሳተፈ ስልጠናዊ ግምገማ ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም አስታውቋል፡፡

በመጨረሻም ለኮሚሽኑ ስራ መሳካት ህብረተሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እያደረጉለት ላለው ቀና ትብብር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምስጋናውን አቅርቦ፤ ነዋሪው በአገልግሎት አሰጣጥም ይሁን የስነ-ምግባር ችግር ያለባቸው የፖሊስ አባለት ሲያጋጥሙት በየአካባቢው በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ፣ ፖሊስ መምሪያዎች እንዲሁም ፖሊስ ኮሚሽን ድረስ በአካል በመቅረብ እንዲሁም በነፃ የስልክ መስመር 991 ወይም 01-11-11-01-11 ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል አስታውቋል፡፡ 

 አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብና መንግስት የጣሉበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ለመወጣት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም