በምእራብ ጎንደር የመከላከያ ሰራዊቱ ግድያ ፈፅሟል በሚል የተሰራጨው መረጃ ያልተጣራ ነው – የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም

628

አዲስ አበባ  ጥር 3/2011 በአማራ ከልል ምእራብ ጎንደር ሰሞኑን ከተከሰተው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ መከላከያ ሰራዊቱ በህዝብ ላይ ግድያ ፈፅሟል በሚል የተሰራጨው መረጃ የተሳሳተና ያልተጣራ መሆኑን የአገር መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

በምእራብ ጎንደርና ምእራብ ኦሮሚያ ክልል ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹምና ኦፐሬሽን ኃላፊ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በምእራብ ጎንደር የሰው ህይወት የጠፋበት አጋጣሚ የተከሰተው የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት በአካባቢው የግንባታ ፕሮጀክት ያካሂድ የነበረውንና ሱር ኮንስትራክሽን የተሰኘ ኩባንያ ንብረት የሆኑ 30 ማሽኖችን የጫኑ ተሽከርካሪዎችን አጅቦ ወደሌላ አካባቢ ሲንቀሳቀስ በነበረበት ወቅት ነው።

ጭነቱ ሸዲ የሚባል አካባቢ ሲደርስ ነዋሪዎች ከኩባንያው ጋር አለን ከሚሉት ቅሬታ ጋር በተያያዘ ጭነቱን ከጉዞ በማስቆም እንዲፈተሽላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ አጃቢው ሰራዊት በመቀበል አስፈትሾ ያለፈ ቢሆንም በሌላ ቦታ ላይ ተሽከርካሪዎቹ እንዲቆሙ መደረጉን ጀነራሉ ጠቅሰዋል።

በዚህ ወቅት አጃቢው ኃይል ጉዞውን በመግታት ጉዳዩን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ጥረት እያደረገ በነበረበት ወቅት ተራራና ጋራ ላይ አድፍጦ የነበረ ሌላ ታጣቂ ኃይል ተኩስ መክፈቱን አመልክተዋል።

በከፍተኛ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የሚንቀሳቀሰው የአገር መከላከያ ሰራዊት በምንም መልኩ ሰላማዊና ራሱን መከላከል በማይችል ህዝብ ላይ ጥይት ተኩሶ ግድያ አይፈጽምም ያሉት ጀነራል ብርሃኑ ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲጣራ ውሳኔ መተላለፉንም ተናግረዋል።  የሚሰራጨው መረጃ ግን ለአገር የሚጠቅም አይደለም ብለዋል።

ለውጡን ተከትሎ የመጣው የመከለከያ ኃይል ተግባሩን የሚያከናውነው በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው ያሉት ጀነራል በርሃኑ እንዲያም ሆኖ በማጣራቱ መሰረት የሰራዊቱ አባላት ግድያ መፈፀማቸው ከተረጋገጠ መከላከያ ህዝቡን ይቅርታ ይጠይቃል፣ ተጎጂ ቤተሰቦችንም ይክሳል፣ በተግባሩ እጃቸው ባለባቸው አካላት ላይም እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊቱ በምእራብ ጎንደር የገጠመው ይህ ክስተት በትግራይ ክልል ዛላንበሳና ሽሬ አካባቢዎች የሰፈረውን ኃይል  እንቅስቃሴ ለማስቆም በህፃናትና ወጣቶች ከተሞከረው ተግባር ጋር የተለያየ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ጀነራሉ እንዳሉት የዛላንበሳና ሽሬ ተቃዋሚዎች የሰራዊቱን እንቅስቃሴ ለመግታት የተገደዱት በህዝብ ጥቅም ስም የተደበቀ የፖለቲካ ዓላማን ማስተጋባት በሚሹ ሌሎች ቡድኖች በተፈጠረባቸው አላስፈላጊ ስጋትና ፍርሃት ሳቢያ ነው። 

እነርሱ የሚያቀርቡት አንዱ ስጋት ጎረቤት አገር ሊወረን ይችላል የሚል እንደሆነም አንስተዋል። ይህም ቢሆን በሌላ የፖለቲከኞች ቡድን የተሰጣቸው አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል።

ያም ሆኖ እነዚህ ወጣቶች ጉዳዩን በአንክሮ ከተመለከቱት በኋላ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር ቅርበት መፍጠራቸውን፣ በተግባራቸው በመፀፀትም ይቅርታ መጠየቃቸውን አንስተዋል።

የፖለቲካ ነጋዴዎቹ ግን ህዝቡን ረግጠን በማለፍ ህዝብንና መንግስትን የማጋጨት ዓላማ እንደነበራቸውም ገልፀዋል። ይህም ወደፊት መጋለጡ እንደማይቀር ነው ጀነራሉ የጠቀሱት። 

ሰራዊቱ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቦ ተግባሩን ለሌላ ጊዜ ያዛወረው ምንም ዓይነት የሰው ህይወት መጥፋት የለበትም ከሚል እምነት ብቻ ሳይሆን ተግባሩ ሌላ ጊዜ ቢተላለፍ የሚያመጣው አገራዊ ጉዳይ አነስተኛነትን በመመዘን ጭምር ነው ብለዋል። 

በምእራብ ጎንደር በተለይም ከመተማ አስከ ጭልጋ ያለው ቦታ ከቅማንት ማንነት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር ያለበት ከመሆኑም በላይ ሽፍታዎች የሚንቀሳቀሱበት፣ ለመንግስት አስተዳደር እንቅፋት የሆኑ  የሚንቀሳቀሱበትና ከፍተኛ  የፀጥታ ችግር ያለበት መሆኑን የጠቀሱት ጀነራሉ ይህ ስፍራ ከሽሬና ዛላንበሳ በፍፁም የተለየ ነው ብለዋል። 

የአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የሚንቀሳቀሰው በከፍተኛ ዲሲፕሊንና ህግ ነው ያሉት ጀነራል ብርሃኑ ሰራዊቱ ምንም ዓይነት ጥይት አልተኮሰም ለማለት ቢያዳግትም ጉዳዩ በጥንቃቄ ሊመረመርና ጥፋተኛው ሊለይ ይገባል ባይ ናቸው፡፡

ጀነራል በርሃኑ በትግራይ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ሰራዊት የመንቀሳቀስ ሥራ የሚካሄደው በሰራዊቱ ውስጥ ከሚካሄደው አጠቃላይ የሪፎርም ሥራ ጋር በተያያዘ መሆኑን ገልፀዋል።