የትግራይ ክልላዊ መንግስት ለህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ መጠናከር ይሰራል…ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

126

መቀሌ ጥር 3/2011 የትግራይ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ያለውን አስተማማኝ ሰላም ከማስቀጠል በተጨማሪ ህገ-መንግስቱና የፌዴራል ስርዓቱን ማስጠበቅ ዋነኛ አጀንዳው መሆኑን ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ዶክተር ደብረፅዮን ገለጹ።

ምክትል ርእሰ-መስተዳድሩ ዛሬ ከሰአት በኋላ በአገራችን ከሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና  የሃገር ሽማግሌዎች ጋር በሰላም ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የትግራይ ህዝብ ከተለያዩ አካላት የተለያዩ ጫናዎች እየደረሱበት መሆኑን ገልጸው በሀገራችን እየተፈጠሩ ያሉት ችግሮች ከትግራይ ጋር የማገናኘት አዝማሚያ እየተለመደ መምጣቱን ተናግረዋል።

“አጀንዳችን ሰለማችንን ማስጠበቅ እንዲሁም ህገ-መንግስቱንና የፌዴራል ስርዓቱ እየደረሰበት ካለው ችግር ማዳን ነው” ብለዋል።

በክልሉ ወሰንን በማሳበብ ጥቃት ለመፈጸም የሚደረጉ ሙከራዎች የተጀመረውን የፀረ-ድህነት ትግሉንና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከመቅረፍ ወደኋላ የማይመልስ መሆኑንም አስረድተዋል።

“በአገራችን እየታየ ያለው የሰላም መደፍረስና የሰዎች መፈናቀል የስልጣን ጥመኞች በሆኑት የሚነሳ እንጂ ህዝብ ለህዝብ በሚፈጥረው ግጭት አይደለም” ብለዋል።

ችግሩ በሀገራችን ያለው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በአግባቡ ወደ ህዝብ ካለመስረጹ የመጣ መሆኑን የገለጹት ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ ለዚህም “በየደረጃው ያለን አመራሮች ተጠያቂ የሚያደርገን ነው” ብለዋል።

በትግራይ ከጫፍ እስከ ጫፍ የተረጋጋ ሰላም መኖር ሌላ ምክንያት ሳይሆን ሁሉንም ነገር በትእግስት ለማሳለፍ ስለሚፈለግ መሆኑን ገልጸው “ይህም በጅምላ ከመፈረጅ ወጥቶ ሊመሰገን ይገባዋል” ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የጀመሩት ጥረት የትግራይ ህዝብና ክልላዊ መንግስቱ ለሰላም የሚሰጡትን ትርጉም ስለሚረዱ ከጎናቸው የሚሰለፉ መሆናቸው ዶክተር ደብረፅዮን አረጋግጠውላቸዋል።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁእ አቡነ ማትያስ፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፊኤልና ሌሎች የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁእ አቡነ ማትያስ እንደተናገሩት የሰው ልጆች ሰርተው ለመግባትም ሆነ እምነታቸውን ለማራመድ ሰላም እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።

ስለዚህም የኃይማኖት አባቶች በዚህ ረገድ ያለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካርዲና ብጹዕ አቡነ ብርሃነእየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው ሰላምን የማስፈን ጉዳይ ለፖለቲካ መሪዎች ብቻ የሚተው እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የኃይማኖት አባቶች የዕምነት ልጆቻቸውን የማግኘትና የመምከር እድልና ኃላፊነት ስላለባቸውም በሁሉም ቦታ በመገኘት ይሔንኑ የሰላም ተልዕኮ እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ ከተገኙት የሀገር ሽማግሌዎች መካከል ወይዘሮ ማሪያ ሞኒር እንደገለፁት ሰላም ሲደፈርስ በቅድሚያ የምትጎዳው እናት መሆንዋን በመጥቀስ የሃገሪቷ ሁኔታ ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳያመራ የፖለቲካ መሪዎች በዋነኛነት ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

አገራችን ባለፉት አመታት በአለም ፈጣን እድገት ከሚያስመዘግቡ አገራት አንዷ ከመሆን አልፋ ለሌሎች አገራት በሰላም አስከባሪነቷ ስትታወቅ መቆየቷን የገለጹት ደግሞ ሌላው የሃገር ሽማግሌ አባቢያ አባጆቢር ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም