ሸኔ የተሰኘውን የኦነግ ክንፍ ትጥቅ የማስፈታት እርምጃ ተጀመረ

794

አዲስ አበባ  ጥር 3/2011 ሸኔ የተሰኘውና በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ክንፍን ትጥቅ የማስፈታት እርምጃ መጀመሩን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ቡድኑ በምእራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች እየፈጸመ ካለው ፀረ-ሰላም ተግባር ህዝቡ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን በወሰደው እርምጃ ከፍተኛ መሻሻል መምጣቱንም የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ይዞ የመንቀሳቀስ ህገ መንግስታዊ ፍቃድ ያላቸው አካላት የአገር መከላከያ ሰራዊት፤ የፌዴራልና የክልል ፖሊስ አባላት ብቻ መሆናቸውን የጠቀሱት ጄነራሉ ከዚህ ውጭ በአገሪቷ የትኛውም አካል ለምንም ዓይነት ዓላማ የጦር መሳሪያ ታጥቆ እንዲንቀሳቀስ አይፈቀድም ብለዋል። 

በአሁኑ ወቅት ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የጦር መሳሪያ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው የኦነግ ክንፍና የዳውድ ኢብሳ ቡድን ሸኔ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

መንግስትም በገባው ቃል ከእነዚህ ሰራዊት አባላት መካከል እንደየፍላጎታቸው ወደ ልማት፣ ወደ መንግስታዊ መዋቅርና የፀጥታው ኃይል ውስጥ ለማስገባት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የገለፁት ጄነራል ብርሃኑ፤ ሆኖም ግን ቡድኑ በሌሎች አካባቢዎች ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎቹን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲገቡ አላደረገም ብለዋል።

 ቡድኑ የሰላምን አስፈላጊነት ተቀብሏል፤ በመሆኑም ጊዜ መስጠት ተገቢ ነው በሚል መልካም አስተሳሰብ በመንግስት በኩል ተይዞ መቆየቱን የጠቀሱት ጄነራሉ፤ ይህም ዋጋ አስከፍሏል ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ቡድኑ ሌላ አዲስ ኃይል መመልመልና ማሰልጠን ላይ መጠመዱን ያነሳሉ።

ያገኙትን ይህንን ጊዜ በመጠቀም ኃይላቸውን ያጠናከሩት የቡድኑ አባላት በህዝብ ላይ በደል መፈፀም መጀመራቸውንም አንስተዋል ጄነራሉ። በአጠቃላይ የቡድኑ ተግባር “መንግስትን የማታለል ዓይነት ነው” ሲሉም ገልፀዋል።

“ኃይላቸውን ካጠናከሩ በኋላ ፀረ ህዝብ ስራ ነው የሰሩት፤ ለህዘብ እታገላለሁ እየተባለ ለዴሞክራሲ ለነፃነት እታገላለሁ እየተባለ፤ ፀረ ህዘብ ስራ  አይሰራም። ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ይህንን ካደረገ አገር ከመጉዳት አልፎ ራሱንም ይጥላል፤ የታየው ግን መንግስትን ማታለል ይመስላል፤ ነገ ከነገ ወዲያ  በተዋዋልነው በተግባባነው እንጨርሳለን፤ እየተባለ ጊዜ ወሰዱ።”

በዚህም መክንያት ቡድኑ የዜጎችን የእለት ተእለት ተግባር ከማወክ ጀምሮ ግድያን፣ ዝርፊያን እገታንና የመሳሰሉት ተግባራትን በንፁሃን ዜጎች ላይ ፈፅሟል ብለዋል።

“ ህዝቡ ገንዘብ እንዲያመጣ ኮታ እየጣለ፤ ገንዘብ ይሰበስብ ነበር፤ ለኃብታሙም ኮታ ለብቻ ለድሃውም አንደዚሁ ኮታ ሰጥቶ ገንዘብ ይሰበስብ ነበር፤  ሌሎች ይህንን የእርሱን አመለካከት የማይቀበሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያግት ነበረ፣ ያግታል፣ ያስራል፣ ቶርች ያደርጋል፣ ፤ የክልሉን የወረዳና የዞን መዋቅርንም አፍርሷል። “

ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ከዚህ በፊት ለረጅም ጊዜ ለነጻነት የታገለና ለህዝብ የቆመ ነው በሚል እምነትና ድጋፍ  ህዝቡ በከፍተኛ ክብር የተቀበለው ቢሆንም አሁን እየፈጸመ ባለው ፀረ ህዝብ ተግባር ግን ተቆጥቷል።

በመሆኑም በሚፈፀመው ግፍ የተማረረው ህዝቡ ባቀረበው አቤቱታና ባደረገው ከፍተኛ ተሳትፎ ቡድኑ ላይ ውጤታማ እርምጃ መውሰድ መቻሉን ነው ጄነራል ብርሃኑ የገለፁት።

“ህዝቡ መንግስት ለምን አይከላከልልንም የሚል ጥሪ አቀረበ፤ በዚያ ጥሪ መሰረትም አሁን ስራው ተጀምሯል፤ ትጥቅ ታጥቆና ተደራጅቶ ከመንግስት የታጠቁ ኃይሎች ውጭ ማንም እንዲንቀሳቀስ  ህገ መንገስቱ ስማይፈቅድ፤ በዚያ መሰረት ትእዛዝ ተሰጥቶ ህግ አስከብሩ የሚል ትእዛዝ ተሰጥቶ  በዚያ ትእዛዝ መሰረት አሁን ትጥቅ ማስፈታት ጀምረናል፤ ከጀመርን ሁለት ሳምንታት አድርገናል  እነዚያ የተዘጉ ከተማዎቸን ነፃ አውጥተናል፤ የተዘጉ መንገዶች ተከፍተዋል።”

በቡድኑ አባላት የተዘረፉ ንብረቶችን ከማስመለስ ባሻገር ፈርሰው የነበሩትን የመንግሰት መዋቅሮች ወደ ነበሩበት የመመለስ ተግባርም መከናወኑን አስታውቀዋል።

የሰው የህወት ማጥፋትን ጨምሮ በተለያዩ ፀረ ህዝብ ተግባራት የተሰማሩትን የቡድኑ አባላትን በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባርም እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዚህም መሰረት በአሁኑ ወቅት የምእራብ ኦሮሚያ ቀጠና ወደተሻለ ህይወት ተመልሷል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኢማታዦር ሹሙ፤ ህዝቡም እለታዊ ተግባሩን በማከናወን ላይ እንደሆነ አመልክተዋል።

“የቡድኑ አባላትም አፈግፍገው ወደ ጫካ ገብተዋል፤  ሰራዊቱም እየተከታተለ አካላቱን ለህግ በማቅረብ የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባሩን ይቀጥላል፤ ትጥቅ እንዲፈቱም ያደርጋል” ብለዋል።

አካላቱ የበደሉትን ህዘብ ይቅርታ ጠይቀው ከህዝቡ ጋር በመቀላቀል ሰላማዊ ህይወታቸውን አንዲቀጥሉም የሚቻለው ጥረት ሁሉ አንደሚደረግም አመልክተዋል።