የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ የ12ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ

64

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ የ12ቀን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ።

አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰትና አለአግባብ ሃብት በማካበት ወንጀል ተጠርጥረው ነው ዛሬ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት።

አቶ ተስፋዬ  የብሔራዊ መረጃና ደሕንነት አገልግሎት  የስራ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ሰዎች በድብቅ እስር ቤቶች እንዲሰቃዩ እንዲገረፉና ሌሎች ሰብአዊ መብቶቻቸውን እንዲያጡ አድርገዋል በሚል ነው ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ያለው።

ፖሊስ  በአሁኑ ወቅት የምርመራ ጊዜውን የጠየቀው በየቀኑ ጥቆማዎች እየደረሱት በመሆኑ ተጨማሪ የምስክሮች ቃል ለመቀበልና ከቴክኒክ ጋር የተያያዙ ምርመራዎችን ለማድረግ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ የምርመራ ስራዎችን ለማከናወን መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።

የተጠርጣሪ ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ከዋለ 6 ወራት ያለፉ በመሆኑ ፖሊስ እስካሁን ማስረጃዎችን አጠናቅሮ ማቅረብ አለመቻሉን ነው ያስረዱት።

በመሆኑም ተጠርጣሪው የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ተከላካይ ጠበቆች ጠይቀዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ከጠየቀው የ14ቀን ውስጥ 12ቱን በመፍቀድ ለጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ሰኔ 16 ቀን 2010ዓ.ም ጠቅላይ ሚነስትር አብይ አሕመድን ለመደገፍ በወጣው ሕዝብ ላይ በቦንብ ፍንዳታ ወንጀል መዝገብ ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሔደባቸው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም