ዐቃቤ ሕግ በነብርጋዴር ጄነራል ጠና ቁርንዲ መዝገብ በተከሰሱ ስምንት ሰዎች ላይ ክስ መሰረተ

84

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 ዐቃቤ ሕግ በነብርጋዴር ጄነራል ጠና ቁርንዲ መዝገብ በተከሰሱ ስምንት ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን አስታወቀ።

ዐቃቤ ሕግ ዛሬ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት እንዳስታወቀው በዚህ መዝገብ ከተጠረጠሩት 26 ሰዎች ውስጥ በስምንቱ ላይ ክስ መመስረቱን ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው በፍርድ ቤቱ 10ኛ ወንጀል ችሎት ሲታይ የቆየው በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መሆኑ ይታወቃል።

ከነዚሀ ተጠርጣሪዎች መካከል ብርጋዴር ጄነራል ጠና ቁርንዲ፣ ኮሎኔል ሙሉ ወልደገብርኤል፣ ኮለኔል አለሙ ሽመልስ፣ ኮሎኔል  ተከስተ ኃይለማርያም ፣ ኮሎኔል አዜብ ታደሰ፣ ሻለቃ ሰመረ ኃይሌ፣ ሻለቃ ይኩኖአምላክ ተስፋና ሻለቃ ሰለሞን አብርሃ ዛሬ አቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተባቸው ናቸው ።

በመሆኑም አቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ መሰረት ተከሳሾቹ በ10ኛ ወንጀል ችሎት የነበራቸው መዝገብ እንዲዘጋና በ15ኛ ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው በመዝገብ ቁጥር 229443 እንዲታይ ጠይቋል።

በዚህ መሰረትም እነዚሁ ተካሳሾች 15ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን መደበኛ የችሎት ሰዓት በመጠናቀቁ ለሰኞ ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም ክሱ ተነቦላቸው መከላከያቸውን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በተመሳሳይም ፖሊስ በዚህ መዝገብ ውስጥ በተጠረጠሩት ኮሎኔል ግርማይ ታረቀ፣ ሌተናል ኮሌኔል ይስሃቅ፣ ሻለቃ ክንደያ ግርማይ፣ እንዲሁም ኮሎኔል አዳነ አጋርነው ላይ የሚያደረግውን ምርመራ አጠናቆ መዝገቡን ለአቃቤ ሕግ ማስረከቡን አስታውቋል።

በተያያዘም በብርጋዴር ጄነራል በርሃ በየነ፣ በብርጋዴር ጄነራል ሀድጉ ገብረጊዮርጊስና ሌተናል ኮሎኔል አስመረት ኪዳኔ ላይ የክስ መመስረቻ 5 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም