የእንጦጦ ሐመረኖህ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ሙዚየም ነገ ለጎብኝዎች ክፍት ይሆናል

67

አዲስ አበባ  ጥር 3/2011 የእንጦጦ ሐመረኖህ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ሙዚየም ነገ ለጎብኝዎች ክፍት ይሆናል።

የእንጦጦ ሐመረኖህ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ህንፃ ንግስት ዘውዲቱ ያስጀመሩት ቢሆንም እቴጌ መነን የግሪክ የሥነ ህንፃ ባለሙያዎችን በመቅጠርና የህንፃውን ሥራ ራስ ደስታ ዳምጠው እንዲቆጣጠሩት በማድረግ የተገነባ ነው።

በነገው ዕለት ለጎብኝዎች ክፍት የሚሆነው ይህ የእንጦጦ ሐመረኖህ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ሙዚየም በአዲስ አበባ ሰባተኛው ሙዚየም ነው።

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅርስ ጥበቃና የቱሪዝም መመሪያ ኃላፊ መጋቢ ሰላም ሰለሞን እንደገለጹት፤ የሙዚየሙ መከፈት ለጥናትና ምርምር፣ ለአገር ገጽታ ግንባታ እንዲሁም ለቱሪስት መዳረሻነት አስተዋፅኦው የጎላ ነው።

የገዳሙ አስተዳዳሪ አባ ጸባቴ ቆማስ ወልደማርያም አድማሱ በበኩላቸው፤ የሙዚየሙ መከፈት አዲሱ ትውልድ ታሪክን እንዲያውቅ ከማድረግ ባሻገር ለአካባቢው ነዋሪዎችም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ አብራርተዋል።

በሙዚየሙ ካሉ ቅርሶች መካከል የተለያዩ  ጥንታዊ የታሪክ የብራና መጸሕፍት፣ የነገስታት አልባሳትና መገልገያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶች ይገኙበታል።

በተጨማሪም  አትሌት ሻለቃ ሐይሌ ገብረስላሴ  በሲዲኒ  ኦሎምፒክ  ያገኘውን የወርቅ ሜዲሊያ ለገዳሙ በስጦታ ያበረከተ በመሆኑ ይህም ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራትና ለማነቃቃት የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል ።

ነገ ለጎብኝዎች ክፍት የሚሆነው የዚሁ ሙዚየም ምርቃት ሥነ ሥርዓት የኢትዮጵያ ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና በዘርፉ የተሳማሩ ባለድርሻ አካላት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም