ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት የአየርላንድ መንግስት ድጋፉን ይቀጥላል - ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድካር

101

አክሱም ጥር 3/2011 ኢትዮጵያ የዜጎቿን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት መንግስታቸው ደጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድካር ገለጸ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት  በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ታሕታይ ማይጨው ወረዳ  በአይርሽ ኤይድ ፕሮጀክት ድጋፍ የተሰሩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለሁለት ቀናት በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡

በሴፍትኔት መርሃ ግብር የታቀፉ ዜጎች የሰሩዋቸው የአከባቢ ጥበቃ ስራዎች የጉብኝቱ አካል ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድካር  በአይርሽ ኤይድ ፕሮጀክት ድጋፍ የተሰሩ ተቋማትና የአከባቢ ጥበቃ ስራዎች ጥራት ያላቸውና የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት አየሰጡ መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡

የአይርላንድ መንግስት የሚሰጠውን ድጋፍ ተግባር ላይ እየዋለ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥና በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉ ዜጎችን የምግብ ዋስትና እንዲያረጋግጡ የአየር ላንድ መንግስ የሚያደርገው ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

በተለይ የአርሶ አደሩን አኗኗር ለመለወጥ እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገገውን ጥረት  ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድንቀዋል፡፡

የአየርላንድ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕርግ የትግራይ ክልል የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃም ተከስተ የአየርላንድ ህዝብና መንግስት በኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

ባለፉት አመታት በሀገሪቱ ቀጣይነት ያለው ልማት እንዲኖር በድህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎች በሴፍትኔት መርሃ ግብር እንዲታገዙ አይርሽ ኤይድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

በአረንጓዴ ልማት፣ በትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና እና ሴፍትኔት መርሃ ግብር የአየርላንድ መንግስት ለረጅም አመታት ድጋፍ ሲያደርግ እንደቆየ ዶክተር አብረሀም ተናግረዋል፡፡

በታሕታይ ማይጨው ወረዳ የማይ ብራዝዮ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር በርኸ  አሰፋ ላለፉት አምስት አመታት በሴፍትኔት መርሃ ግብር  ተጠቃሚ መሆናቸው ገልጸዋል።

የሴፍተኔት መርሃ ግብር ድሃውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አርሶ አደሩ የአካባቢው አርሶ አደር ማህበረሰቡ በመርሃ ግብሩ ታቅፎ አከባቢውን እያለማ የምግብ ዋስትናውን እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በወረዳው በአየርሽ ኤይድ ፕሮጀክት ድጋፍ የተገነባውን የከዋኒት ቀበሌ የጤና ኬላ ውሰጥ የህክምና አገልግሎት ሲሰጣቸው ያገኘናቸው ወይዘሮ ሙሉ በርሀ  በበኩላቸው በአቅራቢያቸው ጤና ኬላ መሰራቱ እናቶች ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው  ገልጸዋል።

ጤና ኬላ ከመሰራቱ በፊት እናቶች ለህከምና ረጅም ርቀት በመጓዝ ብዙ እንግልት ይደርሳቸው እነደነበር አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድካር  በትግራይ ለሁለት ቀናት ያደረጉት ጉብኝት አጠናቅቀው ዛሬ ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም