የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም የሚያከናወነው ተግባር ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ተባለ

400

አዲስ አበባ  ጥር 3/2011 መንግስት የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያከናውነው ተግባር ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የልማት ተነሺ አርሶ-አደሮች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ የተነሺ አርሶ-አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በዚህ ወር ከአንድ ሺህ በላይ የልማት ተነሺዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።

የልማት ተነሺ አርሶ-አደር ልጅ የሆኑት አቶ ግርማ ሰንበቱ በልማት ከተነሱ በኋላ በቂ መተዳደሪያ ስላልነበራቸው በቀን የጉልበት ሥራ መሰማራታቸውን ይገልጻሉ።

ይሁንና መንግስት በማህበራት ተደራጅተው በሚፈልጉት ሙያ እንዲሰማሩ እያደረገ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የአርሶ-አደር ቤተሰብ አቶ ባህሩ ዓለሙ በአሁኑ ወቅት መንግስት በማህበር ተደራጅተውና ስልጠና ወስደው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ትልቅ ተስፋ እንደሆናቸው ገልጸዋል።

ሌላው የአርሶ-አደር ልጅ ኑር መለስ ደግሞ በፈለጉት የስራ ዘርፍ ተሰማርተው ሊሰሩ መሆናቸው ደስተኛ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የተነሺ አርሶ-አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በበኩሉ በተያዘው ወር 1 ሺህ 230 የልማት ተነሺዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዋቁማ አበበ እንዳሉት የልማት ተነሺዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ተነሺ አርሶ-አደሮችን የመለየት፣ በማህበር የማደራጀትና የብድር አቅርቦት የማመቻቸት ተግባራት ተከናውነዋል። 

እስካሁን በጽህፈት ቤቱ ከሰባት ሺህ በላይ አባ ወራዎች ከአምስት ክፍለ ከተማዎችና ከ31 ወረዳዎች የመለየትና የመመዝገብ ሥራ ተሰርቷል።

በዚህም በ118 ማህበራት የተደራጁ 1 ሺህ 230 የልማት ተነሺ አርሶ-አደሮችን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል።

ስልጠናው በከብት ማደለብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በእንጨትና በብረታ ብረት፣ በጠጠር ማምረትና በንግድ እንዲሁም በሌሎች ሰልጣኞቹ በሚፈልጓቸው ዘርፎች የሚሰጥ ነው።

ስልጠናውን የሚሰጡ ኮሌጆች መለየታቸውንና ከስልጠናው በኋላ የብድርና የግብአት አቅርቦት ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም እንዲሁም ከአዲስ ካፒታል ፋይናንስ አክሲዮን ማህበር እንደተመቻቸ ገልጸዋል።

የልማት ተነሺ አርሶ-አደሮቹ በዋናነት ከኮልፌ፣ ከአቃቂ ቃሊቲ፣ ከየካ፣ ከቦሌና ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ሲሆን በማህበር ከተደራጁት በተጨማሪ ሌሎችንም በከተማ ግብርና ለማሰማራት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህም በቋሚነት የሥራ ዕድል በመፍጠር በዘላቂነት ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ ለማስቻል መሆኑን አብራርተዋል።

የአዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ሥራ አክሲዮን ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መሳይ እንሲኒ እንደሚሉት  በማህበር የተደራጁት ተነሺዎች ስልጠና ወስደው መስራት በሚፈልጉት ዘርፍ ግብዓት፣ የመስሪያ ማሽንና ተሽከርካሪ የሟሟላት ሥራ እየተሰራ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባስቀመጠው የድጋፍ ፓኬጅና መመሪያ መሰረት የግብዓት አቅርቦት ለማከናወን በዝግጅት ላይ ነን ብለዋል።

የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም አክሲዮን ማህበር ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሰረቀ-ብርሃን ዘርዓይ በበኩላቸው በማህበር ተደራጅተውና መስፈርቱን አሟልተው ለሚመጡ የልማት ተነሺ አርሶ-አደሮች እስከ 75 በመቶ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የተነሺ አርሶ-አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በዕድሜ መግፋትና በጤና ችግር ምክንያት ምንም የገቢ ምንጭ ለሌላቸው አርሶ-አደሮች ለመሰረታዊ ፍጆታና ለመጠለያ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።