አብዴፓ አገራዊ ለውጡን ለማራመድ የአመራር ለውጥና ማስተካከያ እያደረገ ነው ፡- የክልሉ መንግስት

46

ሰመራ ጥር 3/2011 የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አብዴፓ)አገራዊ ለውጡን ለማራመድ በክልሉ መንግሥት የአመራር ለውጥና  ማስተካከያ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

ፓርቲው ለውጡን ማራመድ እንደማይችል የተናገሩት ደግሞ  የሰመራ ከተማ  ነዋሪዎችና ምሁራን ናቸው፡፡

የክልሉን መንግስት የሚመራው የአብዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤለማ አቡበከር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ  እንደገለጹት  ፓርቲው ባለፈው ወር ያደረገውን ሰባተኛ ጉባኤውን ተከትሎ የክልሉ አመራር ለውጥ አራማጅ እንዲሆን ምደባና የማስተካከያ ሥራዎች በመከናወን ላይ ነው።

ፓርቲው የክልሉን ሕዝብ በተለይም የወጣቱን ጥያቄዎች ለመመለስ ከክልል እስከ ወረዳዎች ያለውን አመራር ለመተካት እየሰራ መሆኑን  የተናገሩት ኃላፊው፣ "ፓርቲው የተማረ የሰው ኃይል አመራር  እንዲካተት በወሰነው መሠረት 58 በመቶ የሚሆነው ሁለተኛ ዲግሪ በላይ ያለው እንዲሆን ተደርጓል" ብለዋል።

ጉባኤው ፓርቲው ክልሉን በማስተዳደር የነበረበትን የአመራር ውድቀትና ለማስተካከልና የሕዝቡን የልማት፣የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ አቅጣጫ በማስቀመጥ  ምደባውም በዚያው መሠረት እንደተከናወነ ገልጸዋል።

አገራዊ ለውጡን እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን ለማውረድ በሚደረገው እንቅስቃሴ በወረዳዎች ደረጃ የሚታየውን የ103 አመራሮች ጉድለት ለማሟላት ፓርቲው በሚወስነው መሠረት ምደባ እንደሚደረግ አቶ ኤለማ አስረድተዋል።

ምደባው ሴቶችን በአመራር ውስጥ  በማካተትና በኅብረተሰቡ ዘንድ ለሴቶች ያለውን የተሳሳተ አመለካከት በመቀየር  ጭምር እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።

ለውጡን ወደ ክልል መንግሥት ተቋማት በማስገባት የአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች አደረጃጀት መቀየሩን ተናግረዋል።

ተቋማቱም የ100 ቀናት ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ እየገቡ መሆናቸውንና በዚህም በሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ለውጥ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

ፓርቲው በክብር ያሰናበታቸውን ስምንት አባላቱን ወደ ሥራ መመለሱ ትክክል እንደሆነ አመልከተው አባላቱ አቅምና ብቃታቸውን መሠረት በማድረግ የተመደቡት በቢሮ ምክትል ኃላፊነት ደረጃ መሆኑን አስረድተዋል።

በሰመራ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች እንደገለጹት በክልሉ የተመደበው አመራር የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስና ለውጥ ለማምጣት አይችልም፡፡

ክልሉን ባለፉት ዓመታት ሲመሩ የነበሩ  አመራሮችን መልሶ በኃላፊነት መመደብ ተገቢነትና ተቀባይነት እንደሌለውም ተናግረዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ሙሳ አብዱ  የአመራሩን ለውጥ  ግለሰብን ለመጥቀም እንጂ ለማህበረሰቡ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣  በአገር አቀፍ ደረጃ የተከናወነው ለውጥ ወደ እነሱ እንዳልመጣ ገልጸዋል።

ክልሉ ያደረገው ለውጥ የአርብቶ አደሩን ሕይወት ያልለወጠውን የቀድሞ አመራር እንደ መመለስ የሚቆጠርና የወጣቱን ተስፋ ያጨለመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

"ፓርቲው ያስቀመጠው አመራር በአገር ደረጃ የተቀመጠውን ለውጥ ለማስቀጠል ዕውቀትም፣ችሎታውም ሆነ አቅም የለውም " ያሉት ደግሞ አቶ ዑመር መሐመድ የተባሉት ሌላው የከተማው ነዋሪ ናቸው።

ነባሩ አመራር በአግባቡ ሳይገመገም መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎበት ሥልጣኑን እንደተቆጣጠሩ ያመለከቱት  አቶ ዑመር፣የአፋርን ሕዝብ ዋነኛ ችግሮችን ለማቃለል ያልቻለው አመራር በምሁራን፣በወጣቶችና በሴቶች ሳይታይ በፓርቲው አባላት በተደረገ ግምገማ ብቻ መመደቡ አግባብነት እንደሌለው ገልጸዋል።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ አደም ዓሊ በበኩላቸው ፓርቲው አዲሱ አመራር የመለሰው አካል የክልሉን ነባራዊ ሁኔታና የአርብቶ አደሩን ዋነኛ ችግሮች የሚመልስና አገራዊ ለውጡን በክልሉ ማስቀጠሉን እንደሚጠረጠሩ ተናግረዋል።

''ችግሮቻችንን በፈጠሩት አስተሳሰቦች፤ችግሮቻችን  መፍታት አንችልም'' ያሉት አቶ አደም፣የህብረተሰቡን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ያልቻለ አመራር መልሶ ሥልጣን ላይ ማውጣት ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።

ፓርቲው አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠልና የክልሉን ሕዝብ ሕይወት ለማሻሻል  ወጣትና ለውጥ አራማጅ አባላትን ወደፊት እንዲያመጣ  የሚመክሩት ደግሞ ሌላው የዩኒቨርስቲው  መምህር አቶ መሐመድ ዓሊ ናቸው።

የክልሉ ሕዝብ በሥራቸው ውጤት ስላጡበት የማይፈልጋቸውና የወጣቶችን ጥያቄ የማይመለሱ አመራሮች  በአገር ደረጃ የሚፈለገውን ሥር ነቀል ለውጥ በልማትና በመልካም አስተዳደር    ለማምጣት እንደሚያስችለውም አመለከተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም