መሬት ወስደው ወደ ልማት ባልገቡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል - የጊኒር ወረዳ ነዋሪዎች

78

ጎባ ጥር 3/2011 ለግብርና ኢንቨስትመንት በሚል መሬት ወስደው ወደ ልማት ባልገቡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ  በባሌ ዞን የጊኒር ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ለኢንቨስትመንት የወሰዱትን መሬት ባላለሙ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት ሲጠቀሙበት የነበረውን መሬት ለኢንቨስትመንት አገልግሎት እንዲውል ቢለቁም እስካሁን ሳይለማ በመቀመጡ ቅር መሰኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በባሌ ዞን የጊኒር ወረዳ ነዋሪ አቶ ከማል አብዳ እንደገለጹት በአካባቢያቸው በግብርና ኢንቨስትመንት ስም ከስምንት ዓመት በፊት የተወሰደ 350 ሄክታር መሬት ያለአግባብ ታጥሮ መቀመጡን አመልክተዋል፡፡

"መንግስት ይህን መሬት ሲረከበን በአካባቢው ላይ በሚካሄደው የእርሻ ኢንቨስትመንት የቴክኖሎጂ ሽግግር ታገኘላችሁ በሚል ሀሳብ ነበር"  ሲሉ አቶ ከማል ተናግረዋል፡፡

መሬቱን የወሰዱት ባለሀብቶች ወደ ልማት ባለመግባታቸው ቅሬታ እንዳሳደረባቸው የተናገሩት ነዋሪው ጉዳዩ  የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አፋጣኝ መፍትሄ  እንዲሰጡት ጠይቀዋል።

ሌላውነዋሪ አቶ ፈይሳ ከተማ በበኩላቸው ባለሀብቶቹ መሬቱን ሲረከቡ በሚያካሄዱት የእርሻ ስራ ከራሳቸውም አልፈው ለአካባቢው ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ቃል ተግብቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በተከለለው መሬት አጠገብ የእርሻ ስራ የሚያከናዉኑ አርሶ አደሮች ከአንድ ሄክታር መሬት 60 ኩንታል ስንዴ በሚያመርቱበት ወቅት ባለሀብቶቹ የወሰዱትን መሬት ሳያለሙ ለዓመታት ማስቀመጣቸው አገርንም ጭምር የሚጎዳ መሆኑን አስተያየት ሰጭው አመልክተዋል፡፡

ወደ ልማት ያልገቡ ባለሀብቶች የወሰዱትን መሬት እንዲመልሱና  ጥቅም ላይ እንዲውል ጠይቀዋል፡፡

የጊኒር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ  ዳዲ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ አርሶ አደሮቹ ከኢንቨስትመንት መሬት ጋር በተያያዘ ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ጉዳዩን ለዞኑ ኢንቨስትመንት በማሳወቅ  ምላሽ እየተጠባበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በወረዳው መሬቱን ያለአግባብ ከልለው አስቀምጠዋል  የተባሉት ባለሀብቶችን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት በባለሀብቶች ፈቃደኛ አለመሆን ሳይሳካ ቀርቷል ።

የባሌ ዞን ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ስሜ በበኩላቸው በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስምንት ዓመታት በገቡት የኢንቨስትመንት ውል መሰረት 5 ሺህ 589  ሄክታር የግብርና መሬት ያለአግባብ ከልማት ውጭ አጥረው ያስቀመጡ ሰባት ባለሀብቶች  መሬታቸው ተነጥቆ ወደ መሬት ባንክ መመለሱን አመልክተዋል፡፡

ወደ ስራ ላልገቡ አምስት  ባለሀብቶች የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡

ወደ መንግስት የተመለሰው መሬት ለሌሎች ልማታዊ ባለሀብቶችና በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች እንደሚተላለፍ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ቅሬታ የሚያነሳባቸው ሌሎች የኢንቨስትመንት ፕሮጄክቶችን አፈጻጸም በመገምገም ለዞኑ ኢንቨስትመንት ቦርድ በማቅረብ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በባሌ ዞን ባለፉት ዓመታት ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዘገብ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት 149 ባለሀብቶች መካከል ከ80 በመቶ የሚበልጡት በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ናቸው ።

በግብርና ኢንቨስትመንት 12 ሺህ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩን ከዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም