የመንገድ ዘርፍ ጠንካራ የፕሮጀክት አስተዳደር ያስፈልገዋል- የዘርፉ ባለሙያዎች

629

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 መንግስት ለመንገድ ዘርፍ የሚያወጣውን ከፍተኛ በጀት በአግባቡ ለመምራት ጠንካራ የፕሮጀክት አስተዳደር እንደሚያስፈልገው ተገለጸ።

የመንገድ ዘርፉን የፕሮጀክት አስተዳደር ለማጠናከር የሚያስችል በዘርፉ ለተሰማሩ መሃንዲሶች በአሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷል።

በአሜሪካ ሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ‘አፍሪካውያንን ማስተማርና ማገልገል’ ከሚበላው ድርጅት የመጡት አቶ ሳምሶን ደምሴ እንደሚሉት በአገሪቷ የመንገድ ግንባታ የሚታየውን የጥራት፣ መጓተትና በተያዘለት ዋጋ አለመጠናቀቅ ችግሮችን ለመፍታት የሰው ኃይሉን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መምራት ያስፈልጋል።

በመንገድ ግንባታ ላይ ሰርቶ ማረም ከፍተኛ ዋጋን እንደሚያስከፍል የሚታወቅ ሲሆን ስልጠናው ነገሮችን በአግባቡ ተረድቶና መርቶ የማያዳግም ስራ ለመስራት ያግዛልም ብለዋል።

በተለይ በመንገድ ግንባታ ላይ አገራት የሚያፈሱትን መዋዕለ-ንዋይ በአግባቡ ለመምራት የባለሙያውን አቅም ማሳደግ ይገባል ብለዋል። 

በአገሪቷ የመንገድ ግንባታ ላይ እየታዩ ያሉ የመዘግየት ችግሮች ከእውቀትና ከልምድ ማነስ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ተናግረዋል።

ይህንንም ችግር ለመፍታት ዓለም አቀፍ ተሞክሮ መቅሰምና የሰው ኃይሉን በስልጠናና በትምህርት ማሳደግ እንዲሁም ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ተሞክሮን መቅሰም ያስፈልጋል ።

እየተሰጠ ያለው ስልጠናም ባለሙያዎች ከስራቸው ያሉ ባለሙያዎችን በአግባቡ በመምራት የመንገድ ዘርፍ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግዋል።

ሰልጠናው ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን  በቀጣይም በተለያየ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሙያዎች የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።