በኦሮሚያ በተለያዩ ዞኖች የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ መካሄድ ጀምሯል

807

ነገሌ/መቱ/ነቀምት  ጥር 3/2011 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 86 ሺህ  ሄክታር መሬት ላይ የሚካሄድ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ትናንት መጀመሩን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በኢሉአባቦርና ምስራቅ ወለጋ ዞኖችም በ332 ሄክታር መሬት ላይ ስራውን ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል ።

በጉጂ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ባለሙያ አቶ ዳንኤል ቴኖ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ትናንት የተጀመረው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ 172 ተፋሰሶችን መሰረት በማድረግ የሚካሄድ ነው ።

“ልማቱ የሚካሄድባቸው የተፋሰሳማ አካባቢዎች በሰውና እንስሳት ንክኪ እንዲሁም ለአፈር መሸርሸርና ለአካባቢ መራቆት አደጋ የተጋለጡ ናቸው” ብለዋል ።

በአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራው ከ180 ሺህ በላይ ህዝብ ይሳተፋል ” ያሉት ባለሙያው እርከኖች፣ ክትሮችና ሌሎች ስራዎች እንደሚካሄዱ አስታውቀዋል ።

በኢሉአባቦር ዞን በ131 ሺህ ሄክታር  መሬት ላይ የሚካሄደው የአፈርና ወሀ ጥበቃ ሰራ በመጭው ሳምንት ውስጥ እንደሚጀመር የገለጸው ደግሞ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ነው።

በፅህፈት ቤቱ  የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ሽፋ ጣሂር እንደገለፁት በ13 ወረዳዎች 262 ተፋሰሶችን መሰረት በማድረግ ለአንድ ወር በሚካሄደው የአፈርና ወሀ ጥበቃ ስራ  ከ190 ሺህ በላይ አርሶአደሮች ይሳተፋሉ ።

በልማቱ ከሚካሄዱ ስራዎች መካከል 27 ሺህ 200 የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችና እርከኖች እንደሚካተቱ አመላክተዋል ።

በተጨማሪም ከ15 ሺህ 822 ሄክታር በላይ መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነጻ እንደሚደረግ ቡድን መሪው አስታውቀዋል ።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት በበኩሉ በ201 ሺህ 308 ሄክታር ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ  ሥራ ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን  አስታውቋል ።

የጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደሣለኝ በልአታ እንደገለፁት ስራው ጥር 15 ቀን 2011 አ.ም በ17 ወረዳዎች ይጀመራል ።

“በዞኑ 536 ተፋሰሶች መሰረት በማድረግ ለአንድ ወር በሚካሄደው ስራው የአፈር እርጥበትን የሚጠብቁና የደኖችን መራቆት ለመቀነስ የሚያግዙ ተግባራት ይከናወናሉ ” ብለዋል ።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ በልማቱ  330ሺህ 599 አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ ።