ልዩ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ለመደገፍ የንግዱ ማህበረሰብ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

492

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ህይወት ለማቅናት የንግዱ ማህበረሰብ ቀዳሚ ሚና በመጫወት ማህበራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

ሚኒስቴሩ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ለተለያየ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በአገሪቱ በሚካሄዱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች ውስጥ እንዲካተቱና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከተለያዩ የግል ድርጅቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ መንግስት በአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለልና ድህነትን ለማስወገድ እንዲሁም ህዝብን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

የግል ሴክተሩ፣ መንግስትና የሲቪክ ማህበራት የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍና እንክብካቤ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው።

በአገሪቱ የተለያየ ማህበራዊ ድጋፍ የሚሹ ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናት፣ ለችግር የተጋለጡ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን፣ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ለችግር የተጋለጡ ሴቶችና በልመና የተሰማሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ይገኛሉ።

ለነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ የማድረግ ሃላፊነት የሁሉም ወገን ድርሻ ሊሆን እንደሚገባም ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የግል ዘርፉ የሰራተኞቻቸውን የስራ ሁኔታ የተመቸ እንዲሆንና የሙያ ጤንነትና ደህንነታቸውን በማስጠበቅ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።

ይሁንና በአገሪቱ ከሚገኙ በርካታ ድርጅቶች መካከል ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን የሚወጡት ጥቂቶቹ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙና ልዩ ድጋፍ የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን ህይወት ለማቅናት በሚደረገው ጥረት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ቀዳሚ ሚና በመጣወት ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይ በንግድ፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በእርሻና በሌሎች አገልግሎት ሰጪ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች በአገር ውስጥና በአለም አቀፍ ገበያ ሰንሰለት ከሚያገኙት ስምና ገበያ አኳያ የማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያግዝ ስርአት በመዘርጋት ባለሃብቶች ከሚያገኙት ትርፍ የተወሰነ ፐርሰንት ለማህበራዊ ጥበቃ እንዲያውሉ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በውይይቱ የተገኙ የግል ድርጅቶችም አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በጀመረችው የለውጥ ጎዳና ተሳታፊ በመሆን የሚጠበቅባቸውን አስተዋፆ ለማበርከት  ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በዚህም ማህበራዊ ድጋፍ ለሚሹ ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናት፣ ለችግር የተጋለጡ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን እና የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ጨምሮ ሌሎች ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

በተለይ በማምረቻ እና በአገልግሎት መስጫ አካባቢ ለሚገኙና ልዩ ድጋፍ ለሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች የሙያ ጤንነትና ደህንነታቸውን ባስጠበቀ መልኩ ለመስራት እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመዋል።