በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ሸኔ በተሰኘው የኦነግ ክንፍ ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው

351

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 በዳውድ ኢብሳ የሚመራው  ሸኔ የተሰኘው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ክንፍ በምእራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች እየፈጸመ ያለው ፀረ-ህዝብና ፀረ ሰላም ተግባር ህዝቡ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር  በመሆን ማስወገዱን የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ።

ቡድኑን ትጥቅ የማሰፈታት ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጀነራሉ ተናግረዋል።

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ ከመንግስት ጋር ተስማምቶ ወደ አገር የተመለሰው የዳውድ ኢብሳው ኦነግ የገባውን ቃል ኪዳን በማፍረስ ህዝብናና አገርን በሚጎዳ ተግባር በመሰማራቱ እርምጃው እየተወሰደበት መሆኑን ነው ጀነራሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት።

በአሁኑ ወቅት ቡድኑ አፈግፍጎ ወደ ጫካ እየሸሸ ቢሆንም ሰራዊቱ ህግ የማስከበር ስራውን ከአካባቢው ህዝብና የመንግስት አካላት ጋር በመተባበር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለው ገልጸዋል።

እርምጃው የሚወሰደው በኦነግ ታጣቂዎች የተለያየ ህገ ወጥ አርምጃና ግፍ የተማረረው ህዝብ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በአማራ ከልል ምእራብ ጎንደር ሰሞኑን ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ የአገር መከላከያ ሰራዊቱ በህዝብ ላይ ግድያ ፈፅሟል በሚል የሚሰራጨው መረጃ የተሳሳተና ያልተጣራ መሆኑንም ጀነራሉ አስታውቀዋል።

ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ባለበት በዚህ የአማራ ከልል አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የአገር መከላከያ ሰራዊት በምንም መልኩ ሰላማዊና ራሱን መከላከል በማይችል ህዝብ ላይ ጥይት ተኩሶ ግድያ አይፈጽምም ያሉት ጀነራል ብርሃኑ ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲጣራ ውሳኔ መተላለፉንም አመልክተዋል።

በማጣራቱ መሰረት የሰራዊቱ አባላት ግድያ መፈፀማቸው ከተረጋገጠ መከላከያ ህዝቡን ይቅርታ ይጠይቃል፣ ተጎጂ ቤተሰቦችንም ይክሳል፣ በተግባሩ እጃቸው ባለባቸው አካላት ላይም እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።