ለለውጡ ቀጣይነት የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን – የሰሜን ወሎ ዞን የመንግስት ሰራተኞች

176

ወልድያ ጥር 3/2011 በየተሰማሩበት የስራ መስክ ተግተው በመስራት ለለውጡ ቀጣይነት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ የሰሜን ወሎ ዞን የመንግስት ሰራተኞች ገለፁ።

የመንግስት ሰራተኞቹ አሁን እየታየ ያለውን ለውጥ ማስቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በወልድያ ከተማ ውይይት አድርገዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ በረደድ ተሰማ እንደገለፁት በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት በተፈጸመው የአመራር ጉድለት ወልድያና አካባቢው ወዳልተፈለገ የጥፋት አቅጣጫ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።

በተለይም በመልካም አስተዳደር ጉድለትና በሰብአዊ መብት ጥሰት የበርካታ ዜጎች ህይዎት ለከፋ አደጋ ተጋልጦ እንደነበር አመልክተዋል።

አሁን እየታየ ያለው ለውጥ የህዝቡን ተስፋ ያለመለመ ቢሆንም ለውጡን የማይቀበሉ አካላት አሁንም ችግር እየፈጠሩ  መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በተሰማሩበት የስራ መስክ ተግተው በመስራት በአገሪቱ ለተጀመረው የለውጥ ሂደት ቀጣይነት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

”በለውጡ የእስረኞች መፈታት፣ የኢትዮ ኤርትራ እርቀ ሰላም መስፈን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሃገር ውስጥ መጥተው በነፃነት እንዲታገሉና መሰል ለውጦች በእኛ እድሜ የማይታሰቡ ነገር ግን የሆኑ ናቸው” ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ዶክተር አየለ አስማማው ናቸው።

”ለውጡ በማንኛም መንገድ እንቅፋት እንዳይገጥመው የበኩሌን ድርሻ እወጣለሁ” ብለዋል።

”ለውጡ ሃገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረና የብዙሃኑን ተስፋ ያለመለመ ነው” ያሉት ደግሞ አቶ ታምራት ገብረ ስላሴ የተሳሉ ተሳታፊ ናቸው፡፡

አሁን በመንግስት ሰራተኛው እየተስተዋለ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለውጡን የማደናቀፍ እንቅስቃሴ መሆኑን መረዳት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የመንግስት ሰራተኛው በተሰለፈበት የስራ መስክ ሁሉ ስራውን አክብሮ በመስራት የለውጡ አጋር መሆኑን በተግባር ሊያስመሰክር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደ ትንሣኤ መኮንን በበኩላቸው የመንግስት ሰራተኛው በተሰለፈበት የስራ መስክ በትጋት በመስራት ለውጡን ለማስቀጠል የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል።

አሁን ያለው አመራርም በስራ ሂደት የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን በየጊዜው በሕዝቡ እያስገመገመ እንደሚያስተካክል ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ከ29 የዞን ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን በለውጡ የመጡ ትሩፋቶችን፣ ለውጡ ያሉበትን ተጋዳሮቶች፣ የወደፊቱን ተስፋና የመንግስት ሰራተኛው ለሰላም መስፈን የሚኖረውን አስተዋጽኦ ያመላከተ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።