በባህር ዳር 431 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት የጌጠኛ ድንጋይ መንገዶች ግንባታ ተጀመረ

235

ባህርዳር ጥር 3/2011 የባህር ዳር ከተማ 431 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት የተመደበላቸው የጌጠኛ ድንጋይ መንገዶች ግንባታ ዛሬ ተጀመረ።

የመንገዶቹን ግንባታ ስራ በይፋ ያስጀመሩት  የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ ናቸው ።

ከንቲባው በወቅቱ እንደገለፁት በስድስት ክፍለ ከተሞች ግንባታቸው የተጀመረው መንገዶች 9 ነጥብ 3 ኪሎሜትር ርዝመት ያላቸው ናቸው።

“ለነዋሪው የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት መገኛ አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት የመንገዶቹ ግንባታ እንዲጀመር ተደርጓል” ብለዋል ።

ለመንገዶቹ ግንባታ ስራ ማካሄጃ የተመደበው ገንዘብ  ከክልሉ መንግስት፣ ከከተማው አስተዳደር፣  ከህብረተሰቡ መዋጮና ከአለም ባንክ በብድር የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል ።

እንደ ከንቲባው ገለጻ በመንገዶቹ ግንባታ 7 ሺህ 500 ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ ይሆናሉ።

“የመንገዶቹ ግንባታ በበጀት አመቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል ” ያሉት ከንቲባው በተያዘላቸው ጊዜ ገደብና ጥራት እንዲጠናቀቁ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል ።

በከተማው ባለፈው ወር መጀመርያ ላይ  ከ480 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተያዘለት የ 7 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ  መጀመሩን ከንቲባው ጨምረው ገልፀዋል ።

የህዳር 11 ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ዋለልኝ አስማማው በአካባቢው ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ባለመገንባቱ ነዋሪው በበጋ በአቧራና በክረምት በጪቃ ጉዳት ይደርበት እንደነበር አስታውሰዋል ።

“ዛሬ የተጀመረው የመንገድ ግንባታ የህብረተሰቡን ጥያቄ መልሷል” ብለዋል ።

“የተጀመረው መንገድ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን እንወጣለን ” ያሉት ደግሞ የክፍለ ከተማው ነዋሪ አቶ ድረስ ተድላ  ናቸው ።