ዘንድሮ የሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ የጊዜ ገደብ አልተቀመጠለትም-ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ

631

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 በተያዘው ዓመት ይከናወናል ተብሎ የሚጠበቀው የአካባቢ ምርጫ የጊዜ ገደብ እንደልተቀመጠለት ተጠቆመ።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እየተገበረ ባለው የተቋም አደረጃጃት ለውጥ ሳቢያ ለማሟያ ምርጫው የጊዜ  ገደቡን ማስቀመጥ እንዳልቻለም የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በአገሪቷ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ ስድስተኛው የአካባቢ ምርጫ በተያዘው ዓመት እንዲካሄድ  የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያቀረበለትን ጥያቄ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማጽደቁ ይታወሳል።

ሰብሳቢዋ እንዳሉት ምርጫ ቦርዱ በህዝብ ዘንድ አመኔታ ያጣበትን ጉዳይና በገለልተኛነቱ ላይ ያለውን ጥርጣሬ ለማጥራት እንዲሁም በተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለሰ ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው።

ተቋሙም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ስራ የሚሰራበትና ብቃት ያለው የሰው ኃይል እንዲኖረው “ስር ነቀል የለውጥ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል” ብለዋል። 

አብዛኞቹ እንቅስቃሴዎች የህግ ማሻሻያዎች የሚፈልጉና ሰፊ ጊዜ የሚወስዱ በመሆናቸውም የተያዙ እቅዶችን አጠናቆ ምርጫው የሚካሄድበት ጊዜ ለመወሰን ያስቸግራል ነው ያሉት።

ውሳኔ የሚጠይቁ ስራዎች በአፋጣኝ መልስ እንዲያገኙና ወደ ምርጫ ዝግጅቱ ለመሄድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የሌሎችን ባለድርሻ አካላትን ድጋፍ እንደሚሹም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

የአካባቢ ምርጫ ማለት በህግ በተደነገገው መሰረት በየደረጃው የሚገኙ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ፣ የማዘጋጃ ቤት፣ የክፍለ ከተማ ወይም የቀበሌ ምክር ቤት አባላት የሚመረጡበት ምርጫ ነው።