ፈረንሳይ የጃፓን ኦሎምፒክ ኮሚቴ ኃላፊ ላይ የሙስና ክስ ልትመሰርት ነው

1193

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 ፈረንሳይ በጃፓን ኦሎምፒክ ኮሚቴ ኃላፊ ላይ በሙስና ወንጀል ክስ ልትመሰረትባቸው እንደሆነ ተነገረ።

የፈረንሳይ ብሔራዊ የፋይናንስ አቃቤ ህግ ቢሮ  በ71 ዓመቱ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ኃላፊ ላይ ከሙስና ጋር በተያያዘ ክስ ሊመሰርት እንደሆነ የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በድረ ገጹ አስፍሯል።

የዜና ወኪሉ ሱንካዙ ታኬዳ ሊከሰሱ መሆናቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ የፈረንሳዩ ዕለታዊ ጋዜጣ ለ ሞንድ ዘግቦት እንደነበር አስታውሷል።

ሱንካዙ ታኬዳ የተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ከጃፓን የ2020 ኦሎምፒክ አዘጋጅነት ጋር መያያዙ የተገለጸ ሲሆን ተጠርጣሪው በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡት ምላሽ ይኑር አይኑር በዘገባው አልተጠቀሰም።

የ71 ዓመቱ የጃፓን ኦሎምፒክ ኮሚቴ ኃላፊ ሱንካዙ ታኬዳ የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ በፈረስ ግልቢያ  ጃፓንን በተወዳዳሪነትና በአሰልጣኝነት በኦሎምፒክ ውድድር ላይ ወክለው ተሳትፈዋል።

ጃፓን እ.አ.አ በ2020 የሚካሄደውን 32ኛውን የኦሎምፒክ ውድድር እንደምታስተናግድ ይታወቃል።

የ71 ዓመቱ ሱንካዙ የኦሎምፒክ ውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር ሲሆኑ ጃፓን ውድድሩን እንድታስናግድ ጥረት ሲያደርጉ ከነበሩ ሰዎች መካከል ይጠቀሳሉ።