የኢትዮጵያ የባህል ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ነገ ይከበራል

875

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 የኢትዮጵያ የባህል ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ነገ በእንጦጦ የዳግማዊ አጤ ምኒልክ ቤተ-መንግስት እንደሚከበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

በመርሃ-ግብሩ በአዲስ አበባ ተቀማጭ የሆኑ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮችና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነሮች እንደሚታደሙበትም ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ የነበሩት አቶ መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ የኢትዮጵያ የባህል ቀን አዲስ አበባን ለዓለም ለማስተዋወቅ ታልሞ የተዘጋጀ ነው።

ዝግጅቱ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና በመሆኗ በቅድሚያ በመዲናይቱ ተቀማጭ የሆኑ የአፍሪካ ዲፕሎማቶች ከተማዋን ይበልጥ እንዲያውቁ ለማድረግ መሰናዳቱንም ጠቅሰዋል።

መርሃ-ግብሩ የሚጀምረው የእንጦጦ ተራራን በመውጣት የዳግማዊ አጤ ምኒልክን ቤተ-መንግስትና የእንጦጦን ሙዚዬምን በመጎብኘት እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪ ወደ ወደ ሱሉልታ ያያ መንደር በማምራት የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ታሪክ በአጭሩ የሚያሳይ ሙዚዬም እንደሚጎበኝና የተለያዩ የባህል ሙዚቃዎችና ውዝዋዜዎች እንደሚቀርቡም ተነግሯል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች፤ እንዲሁም ሌሎችም የግልና የመንግስት ተቋማት በመርሃ-ግብሩ ይሳተፋሉ ተብሏል።

መርሃ-ግብሩ በአፍሪካ ዲፕሎማቶች ቢጀምርም በቀጣይ የሌሎች አገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የሚሳተፉበት እንደሚሆን ተገልጿል።