በቄለም ወለጋ በ235 ትምህርት ቤቶች የተቋረጠው ትምህርት ሊጀመር ነው

77

ነቀምት ጥር 3/2011 በቄለም ወለጋ ዞን  በፀጥታ ችግር በ235 ትምህርት ቤቶች የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ስራ የፊታችን ሰኞ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

በዞኑ ከሚገኙ 509 የ1ኛ፣ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በ235ቱ የመማር ማስተማር ስራ መቋረጡ ተገልጻል።

የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋ በሪሶ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት  በበራሪ ወረቀቶችና በማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን   ለሶስተኛ ጊዜ የተላለፈውን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ ትምህርት ቤቶቹ ከታህሳስ 15 ቀን 2011 አ.ም ጀምሮ ስራቸውን አቋርጠው ቆይተዋል፡፡

በትምሀርት ቤቶቹ የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ስራ የፊታችን ሰኞ ለማስጀመር ህብረተሰቡን የማወያየትና የመቀስቀስ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

የደምቢዶሎ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ገመቹ ረጋሣ "የመማር ማስተማሩ ሥራ የተቋረጠው ተማሪም ሆነ ወላጅ ትምህርት ጠልቶ ሳይሆን የአካባቢው የጸጥታ ሁኔታ አስጊ በመሆኑ ነው"  ብለዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኘው አመራር በየቀበሌው በጀመረው ቅስቀሳ በከተማው ከሚገኙ 19 ትምህርት ቤቶች መካከል በ18ቱ ትላንት ተማሪዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

የፊታችን ሰኞ የመማር ማስተማር ስራው ሙሉ በሙሉ ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ስራ አስኪያጁ አመላክተዋል።

የቄለም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሻፌ ዮናስ  ከትላንት በስትያ ጀምሮ የተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ የመምጣት ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን ገልፀዋል።

"ለህብረተሰቡ በተደረገው ቅስቀሳ ትናንት በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ በተገኙ ጥቂት ተማሪዎች የመማር ማስተማር ስራው ተጀምሯል" ያሉት ደግሞ የቄለም መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ዘሪሁን አስፋው ናቸው።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታመነ ሃይሉ በዞኑ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር  በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሥራዎች ላይ አሉታዊ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል።

"የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራ  ጀመረዋል" ዋና አስተዳዳሪው በዞኑ የፀጥታ ችግር በመፍታት ወደ ቀድሞ ሰላማዊ እንቅሰቃሴ ለመመለስ በከተማ አስተዳደር፣ በወረዳና  በቀበሌ ደረጃ  ሕዝባዊ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም