የመከላከያ መማክርት በለውጡና በሠራዊት አሰፋፈር ላይ ተወያየ

72

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 የመከላከያ መማክርት የተፈጸሙ ለውጦችን አጠናክሮ በሚያስቀጥሉ ነጥቦችና በሠራዊቱ አሰፋፈር ላይ መከረ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ፤ መከላከያ ሠራዊት በህጋዊ ማዕቀፎች፣ በአደረጃጀት፣ በአፈጻጸም ብቃትና በትጥቅ በከፍተኛ የለውጥ ጎዳና ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በውይይቱም ይህን ለውጥ በሁሉም ደረጃ ተፈፃሚ ከማድረግና ወደ ታች ከማውረድ አንጻር የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች ፣ የታዩ ክፍተቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ውይይት እንደተደረገባቸውም  የመከላከያ መማክርቱ በመግለጫው አስቀምጧል።

ውይይቱን የመሩት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዠ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው።

የመከላከያ መማክርቱ ፤ መከላከያ እስካሁን ያደረጋቸው የተቋማዊ ማሻሻያ ስራዎች ምን ያህል ርቀት እንደተጓዙ በመገምገም በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው በሚገባ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የሚገነባው መከላከያም የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ቴክኖሎጂን የሚታጠቅ፣ በራሱ አቅም መጠገን፣ ማሳደግ ብሎም መፍጠር የሚችል እንዲሆን በርካታ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተመልክቷል።

መከላከያ ከቴክኖሎጂ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለውና እንደሌሎች ሃገራት ከራሱ አልፎ ለሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች ምንጭ መሆን የሚችል የቴክኖሎጂ ማዕከል እንዲሆን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችም ተገምግመዋል።

በተዋረድ ያለው መዋቅሩም የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ተዋጽኦ የጠበቀ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ጨምሮ የሀገሪቱን ወቅታዊ ውስጣዊና ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ የሠራዊት አሰፋፈር እንዲኖርም በተጀመረመው እንቅስቃሴ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል።

በዚህም የመከላከያ ሠራዊቱ አሰፋፈር ወቅታዊ፣ ተጨባጭና ታሳቢ ስጋትን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚከናወን በመሆኑ ሕብረተሰቡም በዚህ መልኩ እንዲረዳው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም በውይይቱ መነሳቱ መግለጫው አመላክቷል።

የሠራዊቱ እንቅስቃሴ እንደ አዲስ ከማስፈርም ባሻገር ለረጅም ጊዜ በድንበር ምሽግ ውስጥ የነበሩ የመከላከያ አባላትን ወደ ሥልጠናና አቅም ግንባታ ሥራዎች ማስገባት የአጠቃላይ ተቋማዊ ማሻሻያ አካል በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም የመከላከያ መማክርቱ ጥሪ አቅርቧል።

እስካሁን በተሰሩ የሪፎርም ስራዎችም በሁሉም ረገድ መልካም የአፈጻጸም ጅምሮች እንዳሉ የገመገመው መማክርቱ፥ በቀጣይ እነዚህን ለውጦች አጠናክሮ ለመቀጠል የሚስችሉ ሥራዎች እንዲሰሩ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም