ቋሚ ኮሚቴው በምርጫ ቦርድ ድንገተኛ የመስክ ምልከታ አደረገ

1203

አዲስ አበባ ጥር 3/2011 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድንገተኛ የመስክ ምልከታ አደረገ።

የመስክ ምልከታው ዓላማ ቦርዱ የተቋቋመበትን ዓላማ መሰረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና ለአካባቢና ለሟሟያ ምርጫ እየተደረጉ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማየት ነው።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርትኳን ሚዴቅሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ተቋሙን በአዲስ መልክ ለማደራጀት የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

ቦርዱ ከዚህ ቀደም የህዝብ አመኔታ ያጣበትንና ከገለልተኝነቱ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች ከህግ አርቃቂዎች ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያያት የተዘጋጀው ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን አስታውቀዋል።

ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ምርጫ ዝግጅት ለመሄድ የምክር ቤቱን ድጋፍ እንደሚፈልጉም የቦርዱ ሰብሳቢ ጠቁመዋል።

አገር ውስጥ የገቡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ምዝገባ ስርዓት እንዲገቡ ስልጠና መሰጠቱና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ምዝገባና ቁጥጥር ላይ የህግ ማሻሻያ ለማድረግ ጥናትና ምርምር እየተደረገ መሆኑም ነው የተገለጸው።

የቦርዱን አሰራር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማገዝ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ጋር በመሆን ድረ-ገጽ የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

የመስክ ምልከታው እስከ ነገ እንደሚቀጥል ተገልጿል።