ለነቀምቴ ከተማ እድገት መፋጠን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ የከተማዋ ባለሃብቶች ገለፁ

66
ነቀምቴ ግንቦት 18/2010 ለነቀምቴ ከተማ ልማትና እድገት መፋጠን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ  በከተማዋ የሚገኙ ባለሀብቶች ገለፁ፡፡ በከተማዋ ልማት ዙሪያ ትናንት በነቀምቴ ከተማ ውይይት ተካሄዷል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ተመስገን ጉርመሳ በሰጡት አስተያየት የከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት ለባለሃብቱ የሰጠው ትኩረት በአካባቢያቸው ልማት እንዲሳተፉ መነሳሳት ፈጥሮላቸዋል፡፡ ካሁን በፊት በከተማዋ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ባለመሆኑ ውጤታማ እንዳልነበረ አስታውሰዋል። አሁን የተጀመረው የጋራ ውይይት መድረክ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ጠይቀዋል። በተጨማሪም መድረኩ በከተማው የሚታዩ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በማስወገድ ለከተማዋ ልማትና እድገት መፋጠን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ ኢንጅነር ደበላ ቴሦ በበኩላቸው በከተማዋ በነበረ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የተንዛዛ አገልግሎት አሰጣጥ ባለሃብቱንም ሆነ ህብረተሰቡን ሲያማርር ቆይቷል። ከጥልቅ ተሃድሶ ወዲህ ግን አንፃራዊ መሻሻሎች መታየታቸውን ገልጸው ለከተማዋ ልማትና እድገት መፋጠን ባላቸው አቅም ሁሉ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል። በመንግስት ጥረት ብቻ ልማትን ማረጋገጥ አይቻልም ያሉት ኢንጅነር ደበላ አስተዳደሩ የተለያዩ አደረጃጀቶችንና ፎረሞችን በማቋቋም ነዋሪውንና ባለሃብቱን ማሳተፈ እንደሚገባው ጠቁመዋል። በነቀምቴ ከተማ የአባይ ሆቴል ባለቤት አቶ መኮንን ገመዳ የተሃድሶ ለውጡን ተከትሎ የተሾሙ አዳዲስ አመራሮችን በማገዝ ለከተማዋ ልማት መፋጠን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡ በልማት ስራዎች የሁሉንም ህብረተሰብ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች በቅድሚያ ህብረተሰቡ ሊያውቃቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ቦጋለ ሹማ በመድረኩ  ማጠቃለያ እንደተናገሩት አስተዳደሩ ከባለሃብቱና ከህብረተሰቡ ተሳትፎ ወጪ የከተማውን እድገትና ልማት ወደ ፊት ማራመድ አይችልም። በተለይ ባለሃብቶች የስራ እድል ከመፍጠር፣ የከተማዋን ልማት ከማፋጠንና ድህነትን ከማቃለል አንፃር ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተገንዝበው ተሳትፎአቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የመድረኩ አላማም በመንግስት፣ በህዝቡና በባለሀብቶች ተሳትፎ በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስፈጸም እንዲቻል መግባባት ላይ ለመድረስ መሆኑን አስረድተዋል። በመድረኩ ላይ የተሳተፉ ከ200 በላይ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች በኪራይ ሰብሳቢነት፣ መልካም አስተዳደርና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በሚስተዋሉ ችግሮችና በሌሎችም የልማት አጀንዳዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም